====ቡኢ====
በምስራቅ ጉራጌ ዞን የቡኢ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ፅ/ቤት በ2017 ዓ.ም በጀት አመት የተግባር አፈፃፀም ግምገማና የካፒታል ፕሮጀክቶች ምረቃ መርሀ ግብር የከተማው ጠቅላላ አመራርና ባለለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የቡኢ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ፅ/ቤት ኃላፊና ም/ከንቲባ አቶ ዘላለም ባህሩ በተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት የተሰሩ ስራዎችን የሚዳስስ ሰነድ አቅርበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በማዘጋጃ ቤቱ በውስጥ ገቢ አቅምና በማህበረሰቡ ተሳትፎ በተገኙ ገቢዎች ያስገነባቸውን 0.9 ኬ. ሜ የገነት ሰፈር እና የመናኸሪያ መውጫ የጌጠኛ መንገድ ንጣፍ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ በቡኢ ከተማ መናኸሪያ ግቢ ውስጥ የተገነባው ባለ 3 ክፍል ሽንት ቤትና ባለ 3 ክፍል ሻወር ቤት ያስገነባው ግንባታ በማስመረቅ ለአገልግሎት ክፍት ያደረገ ሲሆን የተገነባው የህዝብ ሽንትቤቱንና ሻወር ቤቱ ለባለ ድርሻ አካላት ቁልፍ አስረክባቧል።
እንዲሁም በ2017 በበጀት አመት ፍጥነትና ፍትሀዊነትን ታሳቢ በማድረግ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ማዘመን የኦቶሜሽን ስራ ተግባራዊ ለማድረግ ተቋሙን በዲጅታል አሰራር በመተካት ከዚህ በፊት ይነሱ የነበሩ የተገልጋይ ቅሬታዎችን ማስቀረት መቻሉን ኃላፊው ገልፀዋል።
በተጨማሪም የከተማዋን የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ደረጃ ማሻሻል ከፈታና ጠረጋ እንዲሁም የጉቺ ሞተቢ ድልድይ ግንባታ መሰል ተያያዥ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በበጀት ዓመቱ እንደከተማ የተሰሩ የልማት ስራዎች አንድ ደረጃ የከተማዋን እድገት ማሳደግ የሚችሉ እንደሆኑ ማሳያ ናቸው ብለው በቀጣይም ከመሰረተ ልማት ፍትሀዊነት፣ ከመንገድ መብራትና ውሃ ከዙሪያው ቀበሌዎች ጋር አስተሳስሮ ከማልማት አኳያም አቅዶ መስራት ይገባል ብለዋል።
አቶ ደበበ አዳነ የቡኢ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊና ዋና የመንግስት ተጠሪ በመንግስታና በፓርቲ ቅንጅታዊ አሰራር በከተማዋ በሁሉ አቀፍ መልክ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን አውስተው ዛሬ ለምረቃ የበቁት ፕሮጀክቶችም በከተማዋ በሁሉም መንደሮች ልማትን በማዳረስ የማህበረሰባችንን የሁልጊዜ ጥያቄ የሆነውን ልማት እየመለስን እንደሆነ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የቡኢ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ በለጠ ጫካ ከተማዋ ከአመት አመት ፈጣን እድገት እያስመዘገበች እንደሆነ ተናግረው የማህበረሰቡን የመልማት ጥያቄ ተቀብሎ መልስ መስጠት የሚችል በሀሳብና አመለካከት አንድ የሆነ በተግባር የተፈተነ ጠንካራ አመራር በመኖሩ ከተማዋን ከትላንት ማንነቷ ወደ አሁናዊ ገፅታዋ መቀየርና ወደ ከፍታዋ ማስፈንጠር መቻሉ ስራዎቹ ይመሰክራሉ ብለዋል።
በከተማው ደረጃ እየተመዘገቡ የመጡ ውጤቶችና ለውጦችም በብልፅግና መንግስት መርህ በመከተል አሁን ላይ ከተማውን እየመሩ ያሉ የከተማው አመራር እና በማህበረሰቡ ቅንጅት የመጣ ለውጥ እንደሆነ ገልፀው በየጊዜው እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች በማስቀጠል አላስፈላጊ ከሆኑ በግል ከሚወሩ ወሬዎች ወጥቶ ይበልጥ የከተማውን እድገት ተናበንና ተቀናጅተን እንደሶዶ ማህበረሰብ የምንመኛትና የምናልማት ከተማ በጋራ ማልማት መቻል አለብን ብለዋል።
የተሰራው የመሰረተ ልማት ስራ የኢኮኖሚ አመንጪነት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ እንደሆነ ገልፀው ጌጠኛ ድንጋይ የተነጠፈባቸው ሰፈሮች ለከተማው የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ የንግድ ድርጅቶች በማስፋፋት የከተማው ገፅታ ከመቀየር አልፎ የውስጥ ኢኮኖሚን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አክለውም ክቡር ከንቲባው ከተማዋ በሁሉም መስክ ልማቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አመራሩ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ገልፀው በ2017 በጀት ዓመት ታቅደው ማሳካት ያልተቻሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በዚህኛው አመት ልዩ ትኩረት በመስጠት አመራሩም 7/24 በሚባል ደረጃ በመስራት በሁለንተናዋ የበለፀገች ከተማ ለመገንባት እንደሚሰራም ገልፀዋል ።
በመረቃ መርሃ ግብሩ ላይም አዲስ በተገነቡ የጌጠኛ መንገዶች አካፋይ ላይ የውበት ዛፎች ችግኝ ተከላ ተከናውኗል።
በመጨረሻም በ2017 በጀት ዓመት በ40/60 የማህበረሰብ ተሳትፎን በተለያዩ የልማት ስራዎች ከተማዋን ሲያግዙ የነበሩና የተሻለ አፈፃፀም የነበራቸው መንደሮች እና አካላት እውቅናና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ከ1-3 የወጡ መንደሮች እንደየደረጃቸው ከ50,000 ብር እስከ 150,000 ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘገባው የቡኢ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው ።
ለተጨማሪ መረጃዎች ገፆቻችን ይከታተሉይ