ጥያ አለም አቀፍ ቅርስ
በዓለም ቅርስ ዝርዝር መሠረት እ.ኤ.አ በ2012 በዓለም 936 የዓለም ቅርሶች የተመዘገቡ ሲሆን 725 ባህላዊ 183 ተፈጥሯዊ እና 28 ጥምር ባህላዊ እና የተፈጥሮ ቅርሶች 113 ሃገሮች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ቅርሶች ከሃገር ዉጪ ሌላውን ዓለም በማስደነቅ የዓለም ህዝብ ንብረቶች እንዲሆኑ በዩኔስኮ ምዝገባ የተጀመረው እ.ኤ.አ 1978 ነበር፡፡ 43 ቅርሶችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ሃገር አውሮፖዊቷ ጣሊያን ናት፡፡ ሃገራችን ኢትዮጵያ 9 ቅርሶችን በዩኔሰኮ ዓለም አቀፍ ቅርሰነት አስመዝግባለች እነዚህም፡- የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስያቲያን በ1978 ዓ.ም የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፖርክ በ1978 ዓ.ም ፣ የፋሲል ግንብ በ1979 ዓ.ም የአክሱም ሃውልት በ1980 ፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ 1980ዓ.ም የታችኛው ኦሞ ሸለቆ በ1980 ዓ.ም፣ ጢያ ትክል ድንጋይ 1980 ዓ.ም ፣ የጀጎል ግንብ 2006 ዓ.ም ፣ ኮንሶ ባህላዊ መልከዓ ምድር 2011 ዓ.ም የመሰቀል በአል አከባበር፤የጥምቀት በአል አከባበበር ስነ ስርአት፤የኢሬቻ በአል አከባበርና የፊቼ ጨምበለላ በአል አከባበር ስነስርአት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም የቅርስ መዝገብ ዩኔስኮ ከተመዘገቡላት የተለያዩ ቅርሶች መካከል የጢያ ትክል ድንጋዮች አንዱ ነው፡፡ የጢያ ትክል ድንጋዮች በደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ውስጥ ከአዲስ አበባ 86 ኪ.ሎ ሜትር እንዲሁም ከመልካ ቁንጥሬ 40 ኪ.ሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ጢያ ትክል ድንጋዮች በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው እ.ኤ.አ በ1980 ሲሆን የተመዘገበበት ምክንያት 3 ዋና ዋና ምክንያቶች አሉት እነሱም፡-
1. የጥንት የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት መሆኑ
2. የጥንት የሰው ልጅ የመኖሪያ አካባቢ መሆኑና
3. የጥንት የፈጠራ ውጤት ሆኖ ለዛሬው ትውልድ ፈር ቀዳጅ መሆኑ ነው፡፡
በጢያ ምድር ባረፈው የቀረሶቹ ክልል ከ12ኛው እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የተተከሉ መሆናቸው የሚነገርላቸው ከ700 እስከ 900 ዓመት ዕድሜ ይሆናቸዋል ተብለው የሚገመቱ 41 ትክል ድንጋዮች ይገኛሉ፡፡
ከነዚህም መካከል 5 ሜትር ርዝማኔ ያለው ትክል ድንጋይ ረጅሙ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የዚህ ጉማጅ በአዲስ አበባ ስድሰት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ጊቢ ውሰጥ ይገኛል፡፡
አ/አ ዮንቨርስቲ የሚገኘው ትክል ድንጋይ ጉማጅ
ትክል ድንጋዩቹ ርዝመታቸው የተለያየ ሲሆን በቁመቱ ትንሽ የሚባለው ደግሞ 1 ሜትር ነው፡፡
ድንጋዩቹ የቆሙበት ምክንያት ለሟቾቹ የቀብር ሃውልት እንዲሆኑ ታስቦ ሲሆን የተቀበሩትም ሰዎች በአካባቢያቸው የጀግንነት ተግባር ፈጽመው ያለፋ መሆኑ በተመራማሪዎች ተረጋግጧል፡፡
በነዚህ ታሪካዊ ድንጋዩች ላይ የተለያየ ምስል ተቀርፆባቸው ይታያል፡፡ ሮጀር ጄሶም በተባለ ፈረንሳዊ ዜጋና ዶክተር ካሳዬ በጋሻው በተሰኙ አረኪዮሎጂስቶች እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም በቁፋሮ የተደረገው ምርምር እንዳሳየው ትክል ድንጋዩቹ ያረፋበት ስፍራ የቀብር ቦታ መሆኑን የሚያስረዳ መረጀ ተገኝቷል፡፡ ተመራማሪዎቹ ትክል ድንጋዩቹ ባረፋበት በ264 ካ.ሜ ክልል ወስጥ ቁፋሮ አድርገው 52 አጽሞች አግኝተዋል፡፡ የተቀበሩት ሰዎች ከ18 እስከ 30 የእድሜ ክልል ውስጥ መሆናቸው በአጥኚዎች ተረጋግጧል፡፡ አጽሞቹ እንደሚያሳዩት በአንድ ቀብር ውስጥ ከሁለት በላይ ግለሰቦች የተቀበሩበት የህብረት መቃብር መሆኑ ሲረጋገጥ ፣ አንድ የቀብር ስፍራ ብቻ አንድ ሰው በነጠላ የተቀበረበት ተገኝቷል፡፡
በቀብር ሥርዓቱ ሞቾቹ ቁጢጥ/ቁጭ/ ብለው መቀበራቸው ሲታወቅ አንዱ ቀብር ብቻ ተንጋሎ የተቀበረ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ እንደ አርኪኦሎጂስቶቹ ትንታኔ ቁጢጥ ብለው የተቀበሩት 51 አጽሞች የክርስትና ሐይማኖት ወደ አካባቢው ከመግባቱ በፊት የተከናወኑ ሲሆን ተንጋሎ የተቀበረው አጽም ደግሞ ክርስትና ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ የተፈፀመ መሆኑን ያመለክታል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በተመራማሪዎቹ ቁፋሮ የሰዎቹ አጽም በ2 ሜትር ጥልቀት ላይ የተገኘ ሲሆን ከአጽሞቹ በ 0.5 ሜትር ርቀት ከፊትና በተመሳሳይ ርቀት ላይ ከበስተጀርባቸው የተለያዩ መዋቢያ ጌጣ ጌጦች ተገኝተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የአንገት ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ የእጅ አንባር፣ ዶቃ፣ ጨሌ፣ ባልጩት እና የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶች አብረው ተቀብረው ተገኝተዋል፡፡
በክትል ድንጋዮቹ ላይ የተቀረፀው ምስል ቁጥር እንደየ ድንጋዩ ሲለያይ በአንድ ትክል ድንጋይ ከ1 እስከ 19 የሳንጃ ምስል መቀረፁን የሟቾቹ የጀግንነታቸው ወይም የገደሉት የዱር እንስሳት ብዛት ለመግለጽ እንደተጠቀሙበት መላ ምት ተሰጥቷል፡፡
የክብ ጡት ምስል የተቀረፀባቸው ትክል ድንጋዩች ደግሞ ቀርፁ አነስተኛ ሆኖ የሚታየው ሟቹ ተባዕት መሆኑን ሲገልጽ የክብ መጠኑ የሚተልቅበት የእንስት ፆታን ለማመልከት ነው ተብሏል፡፡
በድንጋዩቹ ላይ ከተቀረፁት ምስሎች መካከል የባህላዊ መንተራሻ ቅርጽና የእንሰት ተክል ምስል ደግሞ ግለሰቦቹ በኖሩበት ጊዜ ይገለገሉበትና ይመገቡበት የነበረውንና የወቅቱ ባህላዊ መገልገያ ቁሶች ምን እንደነበሩ ለማሳየት እንደሆነ የአርኪኦሎጂሰቶች ትንታኔ ያስረዳል፡፡
በጢያና አካባቢዋ ከ6 የማያንሱ የትክል ድጋይ ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡
ከነዚህ መካከል
የሰው ምስል የሚያሳይ የተቀረፀባቸው /Antromorfic Stelae/
የሳንጃ ቅርጽ የተቀረፀባቸው/Sword Stelae/
ምስሎች የተቀረፀባቸው ትክል ድንጋዮች /Figerative Stelae/
የወንድ ብልት ቅርጽ ያለው /Phallic Stelae/
የፊት ማስዋቢያ ምልክት የሚያሳይ ምስል የተቀረፀባቸው /Facial Ritual Mark Stelae/
የከበሮ ምስል ወይም የነጋሪት ቅርጽ ያለው /Drum Stelae/ በመባል ይመደባሉ፡፡
በጢያ መካነ ቅርስ ላይ በብዛት የሚገኙ ትክል ድንጋዩች ጎራዴ መሰል ቅርጽ ያላቸው ሲሆኑ ቁጥራቸው 36 እንደሆነ ከአስርት ዓመታት በፊት በመካነ ቅርሱ ላይ ጥናት ያካሄዱ አርኪዮሎጂስቶች ጽፈዋል፡፡
ከትክል ድንጎዩቹ መካከል 41 በሚሆኑት ላይ የተለያየ ቅርጽ ያላቸው ምስሎች አሉባቸው፡፡ ምስሎቹ የተቀረፁት በአንደኛው የድንጋዩ ፊት በኩል ነው፡፡ በስፋት ድንጋዩቹ ላይ ከተቀረፁት ምስሎች መካከል የጎራዴ ቅርጽ፣ ክብ ወይም ዲስክ ምስል ቅርጽ የእንሰት ተክል የመሰለ ቅርጽና የጎድን አጥንት የሚመስል ቅርጽ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
እነዚህ ትክል ድንጋዩች ቀደም ሲል ተፈልፍለው ወይም ተጠርበው የመጡት በአካባቢው ከሚገኘው አለልቱ ከተባለው ወንዝ ስር ሲሆን ከትክል ድንጋዩቹ በግምት 1 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም የተረጋገጠው አርኪኦሎጂስቶች በስፍራው ባደረጉት ጥናትና በተገኙ ተመሳሳይ የትክል ድንጋይ ቅርፆች ከዚያ ተጠርቦ ለመምጣታቸው ማሣያ ሆኗል፡፡
እያንዳንዱ ትክል ድንጋይ ለመያዣነት የሚያገለልሉ 2 አና 3 ቀዳዳዎች አሉት፡፡ ይህም ከአለልቱ ወንዝ ተጠርቦ እየተጎተተ እስከ ተተከለበት ስፍራ ድረስ የመጣበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
የጎራዴ ምስል ያለው ጢያ ትክል ድንጋይ
ምድረከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም
ኢትዮጵያ ካሏት ጥንታዊና ታሪካዊ ቤተክርስቲያናትና ገዳማት መካከል የምድረ-ከብድ አቦ ገዳም አንዱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ገዳሙ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ አክብሮት የሚሰጠው ቅዱስ ስፍራ በመሆኑ በርካታ በሺዎች የሚቆጠሩ የሃይማኖቱ ተከታዮችና ጎብኚዎች በየዓመቱ ጥቅምትና መጋቢት 5 ቀን በስፍራው ይታደማሉ፡፡ ይህ ገዳም በደቡብ ሸዋ በጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ በሰዋቲና ገዳም ቀበሌ ገ/ማህበር ልዩ ስሙ ምድረ ከብድ በተባለው ቦታ ይገኛል፡፡
ይህ ገዳም ከአዲስ አበባ በ122 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡ ይህም ማለት ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ የሚወስደው ዋናው መንገድ እስከ ቡኢ 104 ኪሎ ሜትር አስፋልት ሲሆን 18 ኪሎ ሜትር ግን ከዋናው መንገድ ወደ ግራ በመታጠፍ ፒስታ /ጥርጊያ/ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡
የአካባቢው አየር ጠባይ ወይን አደጋ ሲሆን ገዳሙ ረጅም ዕድሜ ማስቆጠሩ የተፈጥሮ ዛፎች ማለትም ዕድሜ ጠገብ የሆኑ በወይራ፣ በጽድና በዝግባ የተከበበ ስለሆነ ነፋሻማና ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ አለው፡፡
የምድረ-ከብድ ገዳም በ1014 ዓ.ም በአፄ እንድርያስ ዘመነ መንግስት በግብፃዊው አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ እንደተገደመ ይነገራል፡፡ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ከደቡብ ግብጽ ሜሳ ተብላ ከምትጠራው ቦታ ተወልደው የ3 ዓመት ልጅ እያሉ በአባ ዘመድ ብርሃን አስተዳደር ይመራ ወደነበረው ታላቅ ገዳም መግባታቸውን ገድላቸው ያስረዳል፡፡
በገዳሙ ውስጥ ይሰጥ የነበረውን ማዕረግ ቅስናን ከብፁ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብረሃም እንደ እንጦርስ ሥርዓት አስኬማንና ማዕረግ ቅስና የሚባሉ መንፈሳዊ ትምህርቶችን አጠናቀው በግብጽ ገዳማት ለ300 ዓመታት ተዘዋውረው ማስተማራቸውን ከገድላቸው ለመረዳት ችለናል፡፡
ከዚህ በኋላ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ በ60 አናብስትና በ60 አናብርት በተፈቀደላቸው የብርሃን ሰረገላ ታጅበው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ምድረ-ከብድ ገዳምን ባርከው መግባታቸውን ገድለ ገብረ-መንፈስ ቅዱስ ያስረዳል፡፡
የገዳሙ የምስረታ ጊዜን በተመለከተ የተለያዩ መረጃ ሰጪዎችና የጽሑፍ ድርሳናት በተለያየ ጊዜ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም ግማሾቹ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተመሠረተ ሲሉ የተወሰኑት ደግሞ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚሉም አሉ፡፡
ምድረ-ከብድ የሚለው ስያሜ ምድረ-ከብድ ከሚል የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጓሜውም ጽኑ ፣ ታላቅ ፣ ልዩ፣ ከፍ ያለ ተራራማ ፣ የክብር፣ የከበደ ቦታ ማለት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ጥንታዊ ገዳም ውስጥ የመጀመሪያውን ቤተ-ክርስቲያን ያሠሩት ንጉስ እንድርያስ ሲሆኑ ለገዳሙ መተዳደሪያ ይሆን ዘንድ 280 ጋሻ መሬት መስጠታቸውም ይወሳል፡፡
የገዳሙ ሌላኛው ቤተ-ክርስቲያን በአፄ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት በፊት አውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ የተሠራ ሲሆን ቆርቆሮ የለበሰው ግን በ1920ዎቹ ዓ.ም በንግስት ዘውዲቱ አማካይነት እንደሆነ ይነገራል፡፡
አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ከምድረ-ከብድ ወደ ዝቋላ ይመላለሱበት እንደነበረ የሚነገርለት ዋሻ ከገዳሙ በስተ ምስራቅ በኩል ከቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ዋሻ የአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ሰረገላ ይባላል ብለው መረጃ ሰጪያችን ገልፀውልናል፡፡
አቡነ-ገ/መንፈስ ቅዱስ ለ562 ዓመታት ከቆዩ በኋላ መጋቢት 5ቀን ማረፋቸውና ቀብራቸውም እዛው ምድረ-ከብድ ገዳም ላይ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡
የምድረ-ከብድ ገዳም ብዙ ውጣ ውረድ ያጋጠመው ገዳም ነው፡፡ እነዚህም በአህመድ ግራኝና በጣሊያን ወረራ የደረሰበት ውድመት የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡
በግራኝ ወረራ ወቅት ብዙ ቤተ -ክርስቲያንና ነዋየ ቅድሳት የተቃጠሉበት ዘመን እንደሆነ በታሪክ የምናውቀው ሃቅ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ምድረ-ከብድ ገዳም ተመሣሣይ ጥፋት ደርሶበታል፡፡
ሌላኛው ደግሞ በጣሊያን ወረራ ወቅት ከ300 በላይ የገዳሙ ምዕመናን በውስጡ እንዳሉ በፋሺስቶች እንደታረዱ ይነገራል፡፡ የምድረ-ከብድ አቦ ገዳም ከ970 ዓመት ዕድሜ በላይ ያስቆጠረ ጥንታዊ ገዳም እንደሆነ ይነገራል፡፡
የምድረ-ከብድ አቦ ገዳም የውስጥ ይዘትን ሁኔታ በተመለከተ በጥቂቱ ስናስቃኛችሁ ገዳሙ በጠቅላላው በቁጥር 4 የሚሆኑ አነስተኛ ሊባሉ የማይችሉ ግቢዎች አሉት፡፡
እነዚህም ግቢዎች፡-
1. የቤተ-ክርስቲያን ግቢ፡- ይህ ግቢ ዋና ግቢ ሲሆን ከሁሉም የበለጠ ሰፊ ግቢ ነው፡፡ እንዲሁም ጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን የሚገኝበት ነው፡፡
2. የእንግዳ ማረፊያ /መቀበያ/ ግቢ ፡- ይህ ግቢ የታላላቅ አባቶችና ጳጳሳት መቀበያ /ማረፊያ /ግቢ ነው ፡- ይህ ግቢ አዲስ አበባ በሚኖሩ የአካባቢ ተወላጆች የተሠራ ግቢ ነው፡፡ በዚህ ግቢ ውስጥ 12 የመኝታ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የመታጠቢያ ክፍሎችና የምግብ መመገቢያ አዳራሽ እዚህ ጊቢ ውስጥ ይገኛል፡፡
3. የመምህራን መቀመጫ ግቢ ፡- ይህ ግቢ የጎተራ እና ልዩ ልዩ ሥራዎች የሚከናወኑበት ግቢ ነው፡-
4. የመናኒያን ግቢ ፡- ይህ ግቢ ብዙ ሥራ የሚከናወንበት ሲሆን የጠቅላላው የገዳሙ ማህበረሰብ ምግብ የሚዘጋጅበት ፣ ከብቶችና በጎች የሚረቡበትና እንዲሁም ደናግል መነኮሳት የሚኖሩበት ግቢ ነው፡፡
ትምህርት ለአንድ ሃገር ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት መሠረት መሆኑ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቤተ-ክርስቲያናትና ገዳማት ከጥንት ጀምሮ በተለይ በመንፈሣዊ ትምህርት በማዕከልነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ከዚህም አንፃር የምድረ-ከብድ አቦ ገዳምም የመንፈሳዊ ትምህርት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በዚህ ገዳም ውስጥ የሚሠጡት መንፈሣዊ ትምህርቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
እነዚህም፡- የንባብ ቤት ፣ የአቋቋም ቤት እና የቅዳሴ ቤት ናቸው፡፡
በገዳሙ ውስጥ አብዛኞቹ የታሪክ መዛግብት የተቃጠሉና የተዘረፋ ቢሆንም የተወሰኑ ቅርሶች አሁንም አሉ፡፡ ለአብነት ያህል የአፄ ሚኒልክ መስቀል ፣ ስንክሣር ፣14ቱ ቅዳሴ መፃህፍት፣ ፆመ ድጓ መጽሐፍ ፣ ድጓ መድሐፍ ፣ ግብረ-ህማም ወዘተ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም የቀድሞ መነኮሳዊያን አባቶች ይለብሷቸው የነበሩ ካባዎችም ይገኛሉ፡፡
ወረዳችን ውስጥ ከሚገኙት ጥንታዊ ገዳማት መካከል በየዓመቱ ጥቅምት 5 እና መጋቢት 5 በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበረው የምድረ-ከብድ አቦ ገዳም ዋነኛው ገዳም ሲሆን ገዳሙ በቱሪስቶች በይበልጥ እንዲጎበኝ ያልተሟሉ ነገሮች ተሟልተውና ከዚህ በላይ የማስተዋወቅ ሥራ መሰራት መቻል አለበት፡፡
የምዕራፈ ፃድቃ ቆንዳልቲቲ ባልወልድ ገዳም
የምዕራፈ ፃድቃ ቆንዳልቲቲ ገዳም የተመሠረተው በ12ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነና 850 ዓመት ዕድሜ እንዳለው ይነገራል፡፡ ከስሙ ስያሜ ብንነሳ ስሙ ቆንደል ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ከዚያም በዕምነት ጠንካራ የነበረች ቲቲ የምትባል ሴት በእምነቷ ምክንያት ጣኦት አምላኪዎች እያባረሯት እዚህ ስትገባ ተሰውራ ጠፋችባቸው፡፡ ከዚያም የት ገባች? ሲባባሉ፤ <<ቲቲ ቆንዳል ገባች>> በማለት ተናገሩ በዚያው ቆንዳል ቲቲ ተብሎ መጠራት እንደተጀመረ አባቶች ተናግረዋል፡፡
ገዳሙ ከዝቋላ አቦ፣ ከምድረከብድ አቦ ገባሞች ጋር የማስተካከል ዕድሜ ቢኖረውም ከዕድሜው ጋር ተያይዞ ብዙ አባቶች እንዲገደም ሰፊ ጥረት ቢያደርጉም ጊዜው ባለመሆኑ እስከዛሬ ደርሷል፡፡
ስለ ገዳሙ የሚገልፁ ጽሑፎች ባይኖሩም ስለ ገድሉ የተፃፋ ጽሑፎች በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ልዩ ስሙ ወረቦ ዜና ማርቆስ ገዳም እንዳለ ይነገራል፡፡ ከዚህም ሌላ የገዳሙ ችንሽ ታሪክ ሃይመለል የተሰኘ መጽሐፍ ላይ በትንሹ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡
የዛሬው ገዳም የትላንቱ የቆንዳልቲቲ ቅ/በዓለወልድ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ ብዙ አባቶች ታሪካዊነቱን ጠብቆ እንዲኖር የየበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል፡፡ ከነዚህ መካከል አቡነ ዜና ማርቆስ ጀግናው ባልቻ አባ ነፍሶ ደጃዝማች ሃብተጊዮርጊስ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸል፡፡
በተለይ አቡነ ዜና ማርቆስ የነበራቸው ድርሻ ሰፊ ነበር ፡፡ ከሰሩዋቸው ሥራዎችም መካከል ይህ ቦታ የእምነት ቦታ ሆኖ እንዲቀጥል እዚህ የነበሩ ጣኦት አማኞችን በማባረር ሰፊ ድርሻ ነበራቸው፡፡
የገዳሙ ታምራቶች መካከል ለመግለጽ ያህል፡፡
በዚህ ገዳም ውስጥ የሚኖር ገርደን የተባለ ጣኦት ነበር ይህ ጣኦት አቡነ ዜና ማርቆስ ረገሙትና ሞተ ከዚያም ተቀበረ በኋላም መሬት አልቀበልም ብላ ተፋችው፡፡
ሌሎችም እምነት የጎደላቸው ሲሞቱ መሬት አልቀበልም ብላ ትተፋ ነበር፡፡ ከዚያም አባ ክንፈ ሚካኤል የተባሉ አባት ከምድረ ከብድ አቦ ገዳም መጥተው አንቺ መሬት ተቀበይው ብለው ገዘቷት፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ መሬት ትቀበል ጀመር፡፡
በአንድ ወቅት እዚሁ ጊቢ ውስጥ የነበረ ከሣር የተሰራ ቤተክርስቲያን በሚቃጠልበት ወቅት ለእሳት ማጥፊያ ከጣራ ላይ የወጣ የእንስራ ጠላ ከሰው እጅ አምልጦ ወድቆ ጠላው ሳይፈስና እንስራውም ሳይሰበር ተርፏል፡፡
ፈዋሽና አዳኝ ወደሆነው ፀበሉ ውሰጥ ጣሊያን ሃገራችንን በወረረች ጊዜ ዜግነታቸው ጣሊያናዊ የሆኑ ግለሰቦች ገላቸውን ለመታጠብ ገብተው በዘንዶ እንደተባረሩ የገዳሙ አባቶች ያስረዳሉ፡፡
ዛሬም የመድሃኒዓለም ሰንበቴ ቤት የሆነው በአንድ ወይራ ስር የሚጠጣ ሰንበቴ ቤት በዶፍ ዝናብ ወቅት እንኳን አንድም የዝናብ ጠብታ የማይገባው መሆኑ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ይህ በአሁኑ ሰዓት ያለው ህንፃ ቤተክርስቲያኑ፣ ደጀ ሰላምና ቤቴልሄም ከሳር ቤት ወደ አሁን ወዳለው ህንፃ የተቀየረው በ1946 ዓ.ም ሲሆን ህንፃውም በወቅቱ ያሰሩት ደጃች ባልቻ አባ ነፍሶ ሲሆኑ ያስጨረሱት ደግሞ ፊት አውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡
ህንፃውን ለመገንባት የጣራው ቅጥቅጥና ወጋግራ የመጣው ልዩ ስሙ ወገራም ከሚባል አካባቢ ነበር፡፡ ይህንን ቅጥቅጥና ወጋግራ እዚህ ለማድረስ በወቅቱ የነበሩ 37 ባለአባቶች /አስገባሪዎች/ ተቀባብለው እዚህ አድርሰውታል፡፡ ከዚያም በ1990 ዓ.ም በቀኝ አዝማች ሰብስብ ዑስማን እድሳት ሲደረግለት በመቀጠልም በቀኝ አዝማች ኃይሉ ቃለወልድ ታድሷል፡፡
ገዳሙ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ በመሆኑ የተለያዩ እድሜ ጠገብ የሆኑ የወይራ፣ የጽድ ፣ የዝግባና የተለያዩ የዛፍ ዓይነቶች ይገኙበታል፡፡
የምዕራፈ ፃድቃን ቆንዳልቲቲ ቅ/በዓለወልድ ገዳም ቅርስ
በገዳሙ ውስጥ ካሉ ቅርሶች መካከል የብራና መጽሐፍ ፣ደወል ፣ መስቀሎች ፣ አልባሳትና ወዘተ… ይገኛሉ፡፡
እንደነዚህ ያሉ የወረዳችንን አሃብቶች በመጠበቅና በማልማት ቅርሶቹ እንደተጠበቁ ለመጪው ትውልድ ለማሸጋገር ብሎም በወረዳችን የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር በማድረግ ህዝባችን ከጎብኚዎች በሚገኝ ገቢ ተጠቃሚነቱ እንዲጨምር ማስቻል የሁሉም ህብረተሰብ ተግባርና ኃላፊነት መሆን ይገባዋል፡፡
የጐርደና ሸንጐ የባሕል መተዳደሪያ ሤራ (ደንብ)
መግቢያ
ሶዶ ወረዳ በደቡብ ብሄርብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት በጉራጌ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ነው፤በውስጡም የተለያዩ ብሔረሰቦች በመከባበርና በመግባባት አብረው ይኖራሉ፡፡
በወረዳችን የሚኖረው ሕብረተሰብ የሚተዳደረው በክልሉ ሕገ-መንግስት መሠረት ቢሆንም የጉራጌ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ከአያት ቅድመ አያቱ የወረሳቸው ቀደም ባሉ ዘመናት መንግስት ሳይመሰረትና ሕገ-መንግሥት ሳይቀረፅ ከረጅም ዘመናት በፊት ሕዝቡ ሲተዳደርባቸው ቆይተው እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቁ የራሱ የሆነ ጠንካራ ባሕላዊ እሴቶች ያሉት እና ከአያት ቅድመ አያቱ የወረሳቸው በርካታ ባሕሎች አሉት፡፡ ጠንካራ ባሕላዊ እሴቶች ለመልካም አስተዳደር መጐልበት ለተሻለ ልማትና ለተሻለ ሰላምና ፀጥታ እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፆኦ እያበረከተ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ደግሞ በልማት፣በመልካም አስተዳደር፣በሰላምና ፀጥታ በሕዝቡ ጤንነት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ስለሆነም የተፋጠነና ዘላቂ ልማት ለማምጣት አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለመፍጠር መልካም የሆኑ ባሕሎቹን ጠብቆ ለማቆየት እንዲሁም ጐጂ ልማዳዊ ድርጊትን ለማስቆም የጐርደና ባሕል ሽማግሌዎች ማጠናከርና ደንብ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህ መሠረት የወረዳው ባሕል ቱሪዝምና መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ለጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) ጠብቆ ለማቆየት ከየቀበሌው ሁለት ሁለት ሽማግሌዎችን በማስመረጥ በወረዳ ደረጃ በማወያየትና በተደረሰበት ደረጃ በድጋሚ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) ላይ በማወያየት የሚሻሻለውን በማሻሻልና በማረምና የሀገሪቱ ህገ መንግሰት በማይጻረር መልኩ ታይቶ የተደረሰበት ደረጃ ወደታችኛው አካል ለማድረስና በሰነድነት ለማስቀመጥ እንዲቻል ይህ የጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡
በመሆኑም ይህንን ደንብ ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉም ወገኖች ያላሰለሰ ጥረት ስለሚጠይቅ ለደንቡ ተፈፃሚነት ሁሉም የወረዳው ሕዝብና የብሄረሰቡ ተወላጆች በያሉበት ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡
አንቀፅ 1፡- የጐርደና ሤራ፡- የክስታኔ ቤተ ጉራጌ ባሕላዊ መተዳደሪያ ደንብ ሲሆን በመንደር፣ በቀበሌ፣ በሃገር ደረጃ መሠራታዊ፣ማህበራዊ ግንኙነቶችና ትስስሮችን ለማጠናከር የሚወጣ ደንብ ነው፡፡
አንቀፅ 2፡- የጐርደና ሸንጐ ሤራ አላማዎች፡-
ሀ) የክስታኔ ጉራጌ ሕዝብ ባሕል፣ታሪክና ቋንቋ ለማሳደግና ለመንከባከብ፣
ለ) በአጐራባች ወረዳዎች መካከል የሚፈጠር ግጭቶችን ለመፍታት፣
ሐ) የእድገትና የመልካም አስተዳደር ፕሮጀክቶች በአግባቡ እንዲፈፀሙ ለመደገፍ፣
መ) በወረዳው ውስጥ ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሕግ የማቅረብ እንቅስቃሴን ለማቀናጀት፣
ሠ) የጉራጌ ሕዝቦችን አንድነትና ውህደት ለማጠናከር፣
ረ) በጐርደና ሸንጐ የተነደፉ ባሕላዊ ሕጎች በአግባቡ መተግበራቸው ለመከታተል፣
ሰ) በጐርደና ሸንጐ ቀደም ሲል የሚመረጡት ወንዶች ብቻ እንደሆኑ ይታወቃል፤ይህ ተሻሽሎ በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑ አዋቂና ሕብረተሰቡ የሚያምንባቸው ወጣቶችና ሴቶችንም በማሳተፍ እንዲሆን ለማድረግ ይሆናል፡፡
አንቀፅ 3፡- የጐርደና ሤራ አፈፃፀም ሥርዓትና ተዋረድ፡-
ሀ) የጐርደና ሸንጐ፡- የሁሉም አገር ሽማግሌዎች ጠቅላላ ስብሰባ ነው፡፡
ለ) የአገር ሸንጐ፡- በርካታ ሳቡኘቶችን (ቀበሌዎችን) ያካተተ የሚወክል ነው፡፡
ሐ) የጥብ ሸንጐ፡- የአንድ ጐሳ አባላትን በማሳተፍ የሚካሄድ ነው፡፡
መ) ሳቡኘት፡- ከየትኛውም ጐሳ ሃይማኖት፣ሙያ፣የኢኮኖሚ የኑሮ ደረጃ ያሉ የመንደር ነዋሪዎች ያቀፈ ባሕላዊ ተቋም ነው፤የየራሱም ደንብና መመሪያዎቸን ለሃዘንም፣ለደስታም፣ ለሥራም … ወዘተ. ሊኖረው ይችላል፡፡
አንቀፅ 4፡- ለጐርደና ሸንጐ የሚቀርቡ ጉዳዮች፡-
ሀ) በተለያዩ ክፍለ ሕዝቦች (ጐሳዎች) የሚነሱ ግጭቶች፣
ለ) ሸንጐ ውስጥ ለሚያጋጥሙ የትርጉም ችግሮች፣
ሐ) በማንኛውም ደረጃ ይሁን ከየአካባቢው የተሰጡ ባሕላዊ ውሳኔዎች የመጨረሻ ይግባኝ ሰሚ የጐርደና ሸንጐ ምክር ቤት ይሆናል፣
መ) ሸንጐ በማስፈፀም ረገድ ችግሮች ቢኖሩ በዚህ የጐርደና ሤራ መሠረት መፍትሄ እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል፣
አንቀፅ 5፡- የውሳኔ አሰጣጥ፡-
ሀ) ለጐርደና ሸንጐ ምክር ቤት የሚቀርብ ማንኛውም ጉዳይ በጉባዔው በተገኙ አባላት ውሳኔ ያልፋል ወይም ይወሰናል፡፡
ለ) በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በሁለት የተከፈለ የውሳኔ ሃሳብ ከተከሰተ ሰብሳቢው በሚመርጧቸው ሽማግሌዎች አማካይነት ሊወሰን ይችላል፡፡
አንቀፅ 6፡- ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ በይግባኝ ወደሚቀጥለው ደረጃ መጥቶ የሚታይበት ሁኔታ
ሀ) የሥር ዳኝነት ጉዳይ በማቅረብ ብቻ ሳይወሰን ውሳኔ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ የመከታተል፣ከተወሰነ በኋላም የማስፈፀም ሃላፊነት አለበት፡፡
ለ) በዚህ ጉዳይ ዋስ የነበሩ ሰዎች ዋስትናቸው ሳይወርድ እንዳስፈላጊነቱ ጥሪ ሲደረግላቸው በዳኛው አማካኝነት ይቀርባሉ፡፡
አንቀፅ 7፡- የጐርደና ሸንጐ መሰብሰቢያ ቦታዎች
ሀ) የየአገሩ የጐርደና ሸንጐ መሰብሰቢያ የሚሆነው ጥንት የነበረው ቦታ ሆኖ፣ይህም በሸንጐ አባላት ይወሰናል፡፡
ለ) የክስታኔ ጐርደና ሸንጐ ምክር ቤት መሰብሰቢያ ቦታ የሁሉም አገሮች ማዕከል በሆነው በወረዳው ርዕሰ ከተማ ቡኢ ላይ ሆኖ፣እንዳስፈላጊነቱ በሌሎች ከተሞችም ጭምር ይሆናል፡፡
አንቀፅ 8፡- በቋንቋ ስለመጠቀም
ሀ) ቋንቋ ለአንድ ሕዝብ መግባቢያ፣የሃሳብ መለዋወጫ፣የማንነት መገለጫና የባሕሉም ነፀብራቅ ስለሆነ በሸንጐ ወቅት ቢቻል በክስታንኛ ቋንቋ በተለይም የአክብሮት መገለጫ የሆኑትን (አትርፌ ትረፍ፣ሣር ዪበላ ያበነ) በማለት የነበረውን የአባቶች የሸንጐ ስርዓት በተከተለ መልኩ መሆን አለበት፡፡
ለ) አንድ ቋንቋ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችለው እያንዳንዱ ተወላጅ በቋንቋው የመጠቀም ባሕል ሲያዳብር በመሆኑ የክስታኔ ተወላጅ የሆነ በተቻለው መጠን ቋንቋው እንዳይጠፋ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አንቀፅ 9፡- በጐርደና ሤራ ማዕረግ አሰጣጥ
የክስታኔ ቤተ ጉራጌ የጐርደና ሤራን መስርቶ ራሱን በራሱ ያስተዳደር በነበረበት ወቅት አዝማች፣አበጋዝ በማለት የባሕል መሪ ወይም አስተዳዳሪ ለመሆን አንድ ሰው ይህ ማዕረግ የሚሰጠው በአካባቢው በሥነምግባሩ፣በአስታራቂነቱ፣በሥራ ወዳድነቱ፣በኑሮ የተሻለ፣አዋቂና ታዋቂ ለሆነ እንዲሁም ወስላታን የማይወድ ለሠላም የቆመ የተቸገሩትን የሚረዳ መሆን አለበት፡፡ ዛሬም እነዚህ መሪዎች ባሕላዊ አመራር፣የአስተዳደር፣የዳኝነትና የሽምግልና … ወዘተ. አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ ቀደም ሲል መሪዎቹ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሕዝቡ አገልግሎት ያውሉ ስለነበር ሕዝቡም ነፃ የሙያ፣የጉልበት … ወዘተ. አገልግሎት ያበረክትላቸው ነበር፡፡ ይህም አሁንም መቀጠል አለበት፡፡
አንቀፅ 10፡- ወንጀልን ስለመከላከል
ሀ) መገንታ የጦርነት፣ያለመግባባት፣የግጭት፣የጭቅጭቅ፣የወስላታ ጊዜያዊ ማስታገሻ ወይም መግቺያ ማቆሚያ ባሕላዊ የጐርደና ሥርዓት ነው፡፡
ለ) ሁለት ጐሳዎች ቢጋጩ ጉዳዩ ታይቶ እስኪወሰን ሳይነካኩ አንዱ ባንዱ ላይ ፀብ እነዳይጭር ባለበት እንዲቆይ ወይም አባራሪው በዕግድ እንዲቆም የሚደረግበት፣ወይም ተበዳይ በዳይን አግኝቶ ቢያሳድደውና አምልጦ በዕግዱ ወይም በጥብቁ ቦታው ቢደርስ ጉዳት እንዳይደርስበት የሚጠለልበት ወይም የሚከለልበት ባሕላዊ ሥርዓት ነው፡፡
ሐ) መገንታ የተፈጠረው ማንኛውም ግጭት ስምምነት ለመፍጠር፣ምሕረት ለማውረድ የእፎይታ ጊዜ የሚሰጥ ነው፡፡
መ) አፈርሳታ (አውጫጭኝ) ማንኛውም ወንጀለኛ በጥቆማ ለመለየት የሚያስችል ዘዴ ሲሆን የተለየውም ሰው የማያምን ከሆነ ከእናቱና ከአባቱ ወገን ሁለት ሁለት ዘመዶቹ እንዲምሉለት ያቀርባል፤ከልማሉለት ግን ወንጀለኛ መሆኑ ይረጋገጣል፡፡
ሠ) ዋሪሃ (የምሽት ሸንጐ) በየምሽቱ የአቅራቢያ ጐረቤታሞች የሆኑ አዛውንቶች፣ወጣቶች ቤት ውስጥ በየተራ በመሰብሰብ ስለሥራ፣ስለአካባቢ፣ስለአገር ደሕንነት፣ስለታሪክና ባሕል … ወዘተ. የሚመካከሩበት መድረክ ነው፡፡ ይህም መቀጠል አለበት፡፡ ዋሪሃ የአልኮል መጠጫና የአካባቢ ልማትን ለማወክ መሆን የለበትም፡፡
አንቀፅ 11፡- ወንጀል ነክ ድንጋጌዎች
በክስታኔ ቤተ ጉራጌ ባሕል በሰው ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ የተወገዘ ሲሆን በርቼ (ግፍ) እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡
1. የቤት ቃጠሎ
ሀ) በግፍ ቤት ያቃጠለ ሰው በማስረጃ ተረጋግጦበት (ካመነ) ቤቱ ለተቃጠለበት ብር 100,0000.00 (እንድ መቶ ሺህ ብር) ይከፍላል
ለ) የቤቱ ቃጠሎ በስህተት ወይም ባለማወቅ ሲሆን ብር 50,000.00 (ሃምሳ ሺህ ብር) ይከፍላል፡፡
ሐ) የቤቱ ቃጠሎ በስህተት፣ስህተት ያቃጠለ ሰው ለተቃጠለበት ብር 25,000.00 (ሃያ አምስት ሺህ ብር) ይከፍላል፡፡
መ) እንስሳትና የቤት ቁሳቁስ ከተቃጠሉ ዋጋቸው ተገምቶ ከቤቱ በተጨማሪ ይከፍላል፡፡
ሠ) በቃጠሎ የአንድ ወይም ከአንድ ሰው በላይ አካል ቢጐድል በአካል ማጉደል ወንጀል ሤራ መሠረት በያንዳንዱ ሰው በየደረጃው ይጠየቃል፤ይህም ጉዳዩ ከሕግ ጋር ከተያያዘ በዎማኖ ሤራ ተጠይቆ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
2. የሰብል ማቃጠል፣መንቀልና መቁረጥ፡-
ሀ) ማንኛውም ሰው በቂም በቀልና ፍትሕ ተጓደለብኝ ወይም ተበደልኩ በማለት ሰብልን፣አዝርዕትን፣ቡና፣እንሰትና ባሕርዛፍ … ወዘተ. ማቃጠል ወይም መንቀል የተወገዘ ድርጊት ነው
ለ) ይህን ጥፋት የፈፀመ ያጠፋው ሰብል በሽማግሌዎች ተገምቶ ከብር 90,000.00 እስከ 150,000.00 ለባለንብረቱ ይከፍላል፤አልከፍልም ካለ በሕግ ይጠየቃል፡፡
3. ስርቆት፡-
ሀ) የቀንድና የጋማ ከብት የሰረቀ ለጥቆማ የወጣ ወጪ ካለ በተለይ ከፍሎ በመሥረቁ ከብር 150 እስከ 6000 መቀጫ ይከፍላል፡፡
ለ) ከብቶቹንም ለባለንብረቱ ይመልሳል፣መመለስ ካልቻለ በሽማግሌ በተገመተ የገበያ ዋጋቸው ለባለንብረቱ ይከፍላል ወይም መሰል ከብት ይተካል፡፡
ሐ) ሰብል ወይም የእርሻ ውጤቶችን የሰረቀ ከላይ በተራ ቁጥር ሀ የተጠቀሰው መቀጫ ከፍሎ የሰረቀውን እሕልም በነበረበት ሁኔታ ለባለንብረቱ ይመልሳል፡፡
መ) ትምህርት ቤቶች፣የጤና አገልግሎት ተቋማት፣የመሠረታዊ አገልግሎት መስጫ አውታሮች፣የሕዝባዊ ድርጅቶች፣የእምነት ቦታዎች ንብረት የሰረቀ ሌባ የሰረቃቸውን ንብረቶች ሁሉ እንዲመልስ ሆኖ፣መመለስ ካልቻለ በሽማግሌና በባለሙያ ተገምቶ ለባለተቋሙ ይከፍላል፡፡
4. አካል ማጉደል፡- በክስታኔ ቤተ ጉራጌ የሰውን አካል ማጉደል ከበድ ወንጀልና በርቼ ነው፡፡
አይን ማጥፋት፣ጥርስ መስበር፣ጆሮ ማደንቆር፣እጅና እግር መቁረጥ፣አፍንጫ መቁረጥ፣ምላስ መቁረጥ፣ከንፈር መቁረጥ፣ጣት መቁረጥ፣አባላዘር ማበላሸት ሌሎችም ወንጀሎች እንደየጉዳት መጠናቸው ታይቶ በሽማግሌዎች የተወሰነ ብር ከፍሎ በዎማኖ ሤራ ተወስኖበት ወይም ፀድቆ ክፍያውን ይፈፅማል፡፡
አንቀፅ 12፡- የካ፡- አንድ የክስታኔ ቤተ ጉራጌ ተወላጅ የሆነ ሰው በአካባቢ ሽማግሌ፣በጥብ ወይም በጐርደና ስብሰባዎች በተለያዩ ጉዳዮች እንዲቀርብ ወይም የሚፈለግበትን እንዲፈፅም ሲጠየቅ ቀርቦ የተጠራበትን ጉዳይ ተረድቶ ለሚቀርብለት ጥያቄ መልስ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
ሀ) ተፈላጊው ተወላጅ ወደ ተፈለገበት ጉባዔ እንዲቀርብ መጀመሪያ አንድ ሰው ይላክበታል፣
ለ) በመጀመሪያው ጥሪ ካልቀረበ ለሁለተኛ ጊዜ ሌላ ሰው ተጨምሮ እንዲቀርብ ይጠየቃል፣
ሐ) በሁለተኛውም ጥሪ ካልቀረበ ለሦስተኛ ጊዜ ሌላ ሰው ተጨምሮ እንዲቀርብ ይጠየቃል፣
መ) በሦስተኛውም ጥሪ ካልቀረበ ወይም የሚፈለግበትን ካልፈፀመና ከሸንጐ የተወከሉ ሊያቀርቡት ወይም ሊያስፈፅሙ ካልቻሉ እንደጉዳዩ ሁኔታና ደረጃ ቤቱ ይገባበታል፣
ሠ) ቤት የተገባበት ሰው በድርጊቱ ተፀፅቶ ሽማግሌዎችን በትህትና ካላቀረበ የሽማግሌዎችን መልዕክት ባለማክበሩ ቤቱ ውስጥ ከብት ታርዶ ይበላና ጉዳዩ ይታያል፣
ረ) በእንቢተኝነት ከቀጠለ ግን ሽማግሌዎቹ በሩን፣ደጁን፣አጥሩን ነቅለው የወግዙታል ወይንም ያስጠነቅቁታክ፤በመጨረሻም በፈፀመው ወንጀል ሽማግሌዎቹ ማስረጃ ሆነው በሕግ እንዲጠየቅና እንዲቀጣ ይደረጋል፣
ሰ) እንቢተኛ የሆነውና ከሕብረተሰቡ የተገለለው ተፀፅቶ ይቅርታ ከጠየቀ ባለመቅረቡ በተጠየቀበት ጉዳይ በየደረጃው ታይቶ ብርቱ ቅጣት ይፈፀምበታል፤በየደረጃው ያሉ የጐርደና ሽማግሌዎች ጉዳዩ ታይቶ የተሰጠው ቅጣት በሙሉ መፈፀሙ ሲረጋገጥ ውግዘቱና ማስጠንቀቂያው ሊነሳለትና ከማህበረሰቡ ሊቀላቀል ይችላል፣
አንቀፅ 13፡- ዎማኖ፡- ሌላ ሁለት መጠሪያ ስሞች አሉት፤(ራጋ) እና (ጌፈቼ ሤራ) ይባላል፡፡ ዎማኖ የሚለው ስም የአገር ሽማግሌዎች የወሰኑት ውሳኔ በትክክል ከጐርደና ሤራ ጋር የተጣጣመ መሆኑን የሚመለከቱ ባሕላዊ ዳኞች ይወክላል፤በተለይም የጉዳት ካሳ፣የወጪ መተኪያና ማካካሻን ለዕርቅ ሥርዓቱ መደረግ ያላባቸውን ባሕላዊ ሥርዓቶች በተመለከተ በትክክል መወሰናቸውን ይከታተላል ወይም ያረጋግጣል፡፡ በይበልጥ ደግሞ እውነቱ እንዲወጣና ዕርቁም በዚያው መሠረት መካሄዱን ለማረጋገጥ ጥረት ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም በአንድ ቤተሰብ ላይ ወይም በአንድ አካባቢ የተከሰተን መከራና ክፉ ነገር ያመጣው ምን እንደሆነ ሚስጥሩን ገልፀው ያወጣሉ፡፡
ሀ) የዎማኖ ሽማግሌዎች የአንድ ጉዳይ ማስረጃ ፍለጋ አይሄዱም፣የአገር ሽማግሌዎች ባቀረቡት ማስረጃ መነሻነት ውሳኔያቸውን ያስተላልፋሉ፣
ለ) ዎማኖ ከግለሰብ ጉዳዮች አልፎ አሳሳቢ የሆኑ የጋራ ችግሮችን እንደ የሰብል ውድመት፣ የተፈጥሮ አደጋ መቅሰፍት፣በአንድ አካባቢ የሰዎችም ሆነ የእንሰሳት በብዛት ማለቅ ወይም ሌሎች ለየት ያሉ ክስተቶችን ይመለከታል፤የአካባቢውን ቀደም ያለ ታሪክ ይመረምራል፤ይህን አስመልክቶም የአገር ሽማግሌዎች በጉዳዩ ምን እንዳሉ ይፈትሻል፤ይህ የኋላ ታሪክ የማወቁ ጉዳይ ምን አይነት ባሕላዊ ሥርዓት ይደረግ የሚለውን ለመለየትና በመጨረሻም (ኬርታ) እንዲካሄድ እስከመወሰን ድረስ ሊኬድ ይችላል፣
ሐ) የዎማኖ ሤራ የሚሰጠው (በገንዛደም) ጥብ (ጐሳ) ብቻ ሲሆን አመላመሉም ከገንዛደም ስድስት ሰዎች ይመረጣሉ፤ከተመረጡት ሰዎች በዕድሜ መብሰል በሂደት የፍርድ ሂደቱን ተግባር ይረከባሉ፣ሆኖም በአንድ ጊዜ የሚካሄድ ርክክብ የለም፤አንድ የዎማኖ አባል ይህን አገልግሎት የሚሰጠው የግብርና ሥራውን ጐን ለጐን እየሰራ ነው፣
መ) ዎማኖ በኬላ ከተማ በሚካኤል ቤተክርስቲያን ግቢ በየወሩ ይካሄዳል፤ማንኛውም ሰው ከየትኛውም ጐሳ፣ፆታ፣ሃይማኖት ይምጣ ችሎቱን ይከታተላል፤ውሳኔውንም ይቀበላል፤ ይፈፅማል፣
ሠ) ዎማኖ የሚጀመረው በምርቃት ሲሆን ይህም የሚቀርቡት ጉዳዮች ያለምንም አድልኦ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለማከናወን እንዲቻል ነው፡፡
አንቀፅ 14፡- ጋብቻ ወይም መተጫጨት፡- ጋብቻ የመልካም ኑሮ መሰረትና ቤተሰብን ማስቀጠል የሚችል ሆኖ ክቡር በመሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊደረግለት ይገባል፡፡
ሀ) ጋብቻ የሚፈፀመው በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት ላይ የተመሰረተና የቤተሰብም ፈቃደኝነት ያካተተ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ይሁንና ሁለቱ ተጋቢዎች ቢስማሙና እድሜያቸው ለጋብቻ ከደረሱ ወላጆች መከልከል የለባቸውም፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረግ ጋብቻ የተከለከለ ነው፤የተጋቢዎች ዕድሜም በሕግ መንግስቱ በተቀመጠው መሠረት ነው፣
ለ) ሁለቱ ተጋቢዎች ከመጋባታቸው በፊት የኤች.አይ.ቪ. (ኤድስ) በሽታ ቢያንስ 2 ጊዜ መመርመር ግዴታቸው ሲሆን ቤተሰብም ይህንኑ ማረጋገጥና የምርመራ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፤በምርመራ ወቅትም የሚመጡ ተመርማሪዎች ወደ ምርመራ ጣቢያ ሲመጡ ከሁለቱም ወገን ወንድምና እህት ከሌለም የቅርብ ዘመድ ከተመርማሪዎች ጋር አራት ብቻ ሆነው መገኘት አለባቸው፤ይህንንም ያልፈፀሙ ተጋቢዎች ካሉ ጋብቻ መፈፀም አይችሉም፤ያለመመርመራቸው ከታወቀ ማንም ግለሰብ ወደ ሰርግ ቤት መሄድ የተከለከለ ሆኖ ይህንን ተላልፎ የፈፀመ በባሕላችን መሠረት ደጋሽ ብር 1,500.00 (አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር) ታዳሚው እያንዳንዱ ብር 100.00 (አንድ መቶ ብር) ይቀጣል፣
ሐ) በበሽታው የተጐዱ ወገኖችን ድጋፍና እንክብካብ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ህብረተሰብ ሲሆን የማስተማርና ሳቡኘት (ዕድር) ከሞት በኋላ መቅበር ብቻ ሳይሆን በሕይወት ሳሉ የመርዳት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፣
መ) በከተማ አካባቢ በሥራ ተሰማርተው ያሉ ጥንዶች ወይም ባልና ሚስቶች ከቆይታ በኋላ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) መከላከያ የመጠቀምና የመመርመር ገዴታ አለባቸው፤ይህ ሳይፈፀም ቢቀር በባሕላችን መሠረት ብር 800 (ስምንት መቶ ብር) ይቀጣል፣
ሠ) የቤተ ዘመዶችን መጋባት በባሕልም ይሁን በሕግ የተከለከለ ነው፤በቤተሰብ ሲቆጠር እስከ 7 ቤት ትውልድ ድረስ መጋባት አይቻልም፤ይህንንም ተላልፎ የተገኘ 600 ብር ይቀጣል፣
ረ) የቸግ (ሚጁ) የሚሉ ሌሎችም ከጋብቻ በፊት የሚፈፀሙ ስርዓቶች እንዳሉ ሆነው ወደ ልጅቷ ቤት የሚሄድ ሽማግሌዎች ከሁለት የልበለጡ ሆነው ምንም ድግስ ሳያስፈልግ በአነስተኛ ወጪ በባሕል መስተንግዶ ከ200 ብር ያልበለጠ መከናወን አለበት፤ከዚህ ውጪ የተከለከለ ስርዓት ነው፣
አንቀፅ 15፡- የሚት ደኦት (ጥሎሽ) ፡- ጥሎሽ ለብዙ ጋብቻዎች አለመሳካትና በአቅም ማነስ ምክንያት ጥሎሽ ላለመክፈልና በጋብቻ ሳቢያ ለሚወጣ ወጪ ፍራቻ የጠለፋ መስፋፋትና መንስዔ እየሆነ ነው፡፡ በሌላ በኩል ክቡር ጋብቻውን በገንዘብ አማካኝነት እንደሚፈፀም ተደርጐ በመወሰድ የሁለቱ ተጋቢዎች ቤተሰብ ይህንኑ በመገንዘብ ለጥሎሽ ብር 1000 (አንድ ሺህ ብር) ብቻ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
1. ለሙሽሪት የሚሰጥ ስጦታና አልባሳት በተመለከተ፡-
ጋብቻ የሚመሰረተው ተጋቢዎቹ በቀጣዩም ኑሮዋቸው ላይ ችግር እንዳይፈጠር መታሰብ ስላለበት በሙሽራው መሰጠት ያለበት ከዚህ ውጪ ከላይ የተገለፁት ችግሮች ስለሚያስከትል የተከለከለ ነው፡፡ ይሁንና ከሙሽሪት ወይም ከሙሽራው ከላይ የተጠቀሰውን ባይፈልጉ አይገደዱም
2. ለሰርጉ የሚደረግ ድግስ በተመለከተ፡-
ሀ) ድግሱ የሁለቱ ተጋቢዎች ቤተሰብ አቅም ያገናዘበ መሆን አለበት በወረዳችን ሰርግ መደገስ ባሕላችን ቢሆንም አሁን በሚታየው መልኩ ቤተሰብና ተጋቢዎችን ከመጠን ባለፈ አቅም አሳጥቶ በሚያፈናቅል ሁኔታ በግልፅ እየታየና የተመሰረተውም ትዳር እያፈረሰና በችግሩ ምክንያት ለወንጀል መከሰት መንስዔም ጭምር እየሆነ ከራሱ አቅም ጋር የተመጠነ ያለ ምንም ይሉንታ እና ተፅዕኖ ቤቱ ባፈራው አንሰተኛ መስተንግዶና ወጪ መፈፀም አለበት፤ከአቅም በላይ ድግስ ደግሶ ሕዝብ እየጠሩ ማብላት ክልክል ነው፡፡
ለ) በሰርግ ጊዜ ልጅቷ ቤት ሲኬድ ለሳንቃ መዝጊያ መክፈቻ ተብሎ የሚጠየቅ ብር ወይም ሻሽ ሲጣል የሚጠየቅ ብር ጐጂ ስለሆነ መቅረት አለበት፤ይህን ፈፅሞ የተገኘ በባሕላችን 700 ብር ይቀጣል፡፡
ሐ) ጫጉላም ከሰርጉ ቀን በፊትም ሆነ ኋላ በአግባቡ መሆን አለበት፣
3. የሙሽራው የመንቀሳቀሻ ሠዓት በተመለከተ፡-
በሰርግ ዕለት ያለ ሠዓት በመነሳትና በመንገድ በሙሽራዎችና በአጃቢዎች ላይ እንግልት ከማስከተሉም በላይ የኤች.አይ.ቪ ተጋላጭነትን እያባባሰና ለሌሎች ችግሮች የሚጋብዝ ስለሆነ የጭለማ ጉዞ ባሕልም የሌለን በመሆኑ ሙሽራው ወደ ሙሽሪት ቤት መነሳት ያለበት ከቀኑ 6፡00 ሠዓት ሆኑ ከቀኑ 10፡00 ሠዓት ከሙሽራዋ ቤት መነሳት አለበት፡፡ በጣም የራቀ ከሆነ ሠዓት በማስተካከል ቀደም ብሎ መነሳት አለበት፤ከዚህ ውጪ የተጓዘ በባሕልም ሆነ በሕግ ይቀጣል፡፡
4. አጃቢዎችን በተመለከተ፡-
የአጃቢዎች መብዛት ለሁለቱም ተጋቢዎች ጠቀሜታ የሌለው በመሆኑና የኢኮኖሚ ጫና ስለሚያመጣ ከ15 ሰው ያልበለጡ መሆን አለባቸው፤ከዚህ በላይ ያስከተለም ሆነ የተቀበለ በባሕላችን ወይም በሕግ ይቀጣል፡፡
5. የሙሽሪት የኮሶ ስርዓት፡-
ሀ) የኮሶ ስርዓት ጠቀሜታ የሌለው ስለሆነና አላማውም በጫጉላ ጉዞ ሙሽሪት እንድትደክምና የወንዱን የበላይነት እንዲረጋገጥ ተብሎ የሚደረግ ሲሆን ከጥቅሙም ጉዳቱ ስለሚያመዝን መቅረት አለበት፤ከኮሶ ጋር ተያይዞ የሚደርስ ድግስና ስርቆቸ መቅረት አለበት፤ይህንን ፈፅሞ የተገኘ በባሕላችን (በሕግ) ይቀጣል፡፡
6. ኡርጋ በተመለከተ፡-
በኡርጋ ጊዜ 2ቱ ሙዜዎች ብቻ መሄድ አለባቸው፡፡ ለዚህ ተብሎ ድግስ መደገስ የተከለከለ ነው፤ከሁለቱ ሚዜዎች ውጪ የሙሽሪት ቤተሰቦችም መቀበል የለባቸውም፤ ከዚህ ውጪ የፈፀመ በባሕል (በሕግ) ይቀጣል፡፡
7. አውታ (አፍታ) በተመለከተ፡-
አውታ ወጣቶች ወደ አልተፈለገ ድርጊት እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ በተለይ ሴት ልጆች እየተደፈሩ በመሆኑና ለኤች. አይ. ቪ (ኤድስ) የሚያጋልጥ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ስለሆነም ወንድምና እህት ብቻ ቁጥራቸውም ከ3 ያልበለጠ መሄድ አለባቸው፡፡ ወንድምና እህት ከሌለ 2 ወንዶች ብቻ እንዲጠይቁ መደረግ አለበት በጥየቃ ጊዜ ምንም የተለየ ድግስ መደገስ የተከለከለ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚፈፀም የሙሽራ ቤተሰብም ሆነ ላኪው ቤተሰብ በባሕላችን መሠረት ይቀጣል፡፡
8. ቅቤ መቀባት በተመለከተ፡-
ሀ) ቅቤ መቀባት ለሁለቱም ወገኖች የሚሰጠው ጠቀሜታ ስለሌለና ጉዳቱ ከፍተኛ እየሆነ ስለመጣ ከ5 ሴቶች በላይ መሄድ እንደሌለባቸውና በዕለቱ መመለስ አለባቸው፡፡ ይህን የተላለፈ ብር 2000 (ሁለት ሺህ ብር) ይቀጣል፣
ለ) የአገቡ ሙሽራዎች ወደ አባታቸው ቤት ተመልሰው 3 ወር ይቀመጣሉ፡፡ ይህ አጉል ባሕልና ጐጂ እየሆነ የመጣ ስለሆነ ከባልዋ ጋር ብቻ ለመልስ መጥታ አብራ መመለስ አለባት፤ከዚህ ውጪ ፈፅሞ የተገኘ 300 ብር (ሦስት መቶ ብር) ይቀጣል፣
9. መልስ (አንገትኧግዳን)፡-
መልስ (አንገትኧግዳን) ወቅት የልጅቷ ቤተሰብም ሆነ የልጅ ቤተሰብ ለተጨማሪ ወጪና ጉዳት የሚጋብዝ ነው፡፡ ስለሆነም ሁለቱ ተጋቢዎች ከ2 ሚዜዎቻቸው ጋር 100 ብር (አንድ መቶ ብር) ብቻ በመያዝ በአንድ ቀን ደርሰው መመለስ አለባቸው፡፡ የልጅቷ ቤተሰቦችም በጣም ባነሰ ወጪና ዝግጅት ቤት ያፈራውን ብቻ አዘጋጅተው ሊሸኙ ይገባል፡፡ ምን አልባት እርድ እንኳን ቢያስፈልግ በግ ብቻ አርደው ማስተናገድ አለባቸው ከዚህ ውጪ ይዞ የሄደም ይሁን የተቀበለ በባሕላችን መሠረት የተከለከለና የሚያስቀጣ ነው፡፡ ቅልፈትና ተከቦቸም ከነጭራሹ ጠቀሜታ የሌለው ስለሆነ እንዲቀር ተወስኗል፡፡
10. ከሰርግ ደስታ ጋር በተያያዘ የመሳሪያ ተኩስ በተመለከተ፡-
ከሰርግ ደስታ ጋር በተያያዘ ደስታ ሆነ በሌላ ደስታና እንዲሁም በሐዘን፣በለቅሶ መሳሪያ መተኮስ የተከለከለ ነው፡፡ ይህንን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በባሕላችን ተቀጥቶ መሳሪያው ተወርሶበት ለመንግስት ገቢ ይደረጋል፡፡ ግለሰቡ ከወረዳው ወጪ ቢሆን በህግ ተከሶ ይጠየቃል፡፡ አንቀፅ ሦስትን ጠቅላላ የተላለፈ ብር 1800 (አንድ ሺህ ስምንት መቶ ብር) ይቀጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ ድርጊቱ ከብደት እየታየ ከ15-24 ሽማግሌዎ የካ ተልኮበት ያስተናግዳል፡፡
አንቀፅ 16፡- አዳብና በተመለከተ፡- የአዳብና ስርዓት በአሁኑ ወቅት ድሮ ከነበረው ባሕል በተለየ መልኩ እስከ ማምሻ ድረስ በመቆየቱ ለጠለፋ ለመደፈር ትልቅ በር ከፋች እየሆነ ከመሆኑም በላይ ለኤች. አይ. ቪ. (ኤድስና) ተዛማጅ በሽታዎች መስፋፋትም ትልቅ መንስዔ እየሆነ መጥቷል፤ስለሆነም አዳብና ከነጭራሹ ይጥፋ ባይባልም አዳብናን ጨምሮ ከባሕል ጋር የተያያዙ ጭፈራዎችና ጨዋታዎች እስከ ቀኑ 9፡00 ሰዓት ድረስ ጥበቃ እየተደረገላቸው ማብቃትና መብትን አለበት፡፡ ይህንንም በየአካባቢው ባሉ የባሕል ሽማግሌዎች የመንግሥት አካላት ጭምር በጋራ ጥበቃ እያደረጉለት በሰዓቱ የሚበተኑበት ሁኔታ እየፈጠረ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ያሰማራ አባትና እናትም ሆነ ግለሰብ በባሕላችን መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ አንቀፅ አራትን ተላልፎ የተገኘም እስከ ብር 300 (ሦስት መቶ ብር) ይቀጣል፡፡
አንቀፅ 17፡- ከበድ ያሉ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፡-
ሀ) ጠለፋና ሸኮካንቾ በጤና በአካልና በስነልቦና ላይ የከፋ ጉዳት የሚያስከትልና ትልቅ ወንጀል ስለሆነ የጠለፈ የተባበረና የደበቀ በባሕላችንና በሕግ ይቀጣል፣
ለ) ይህንን ወንጀል የፈፀመ፣የተባበረ በሕግ ቀርቦ እንዲጠየቅ የባሕል ሸንጐ አስፈላጊውን ጥረት ያደርጋል፤በሕግ ለመጠየቅ ያልተሟሉ ነገሮች ካሉ በባሕላችን መሠረት ጠለፋ ፈፃሚውና ተባባሪው ነፃ የሚያወጣቸው 5 (አምስት) ሰዎች እንዲምሉላቸው ተፈቅዶ ነፃ ካለወጧቸው ወይም ካልማሉላቸው ዋና ጠላፊው በባህል ሽማግሌዎች ብር 10,000.00 (አስር ሺህ ብር) ቅጣት ተቀጥቶ ለልጅቷና ለቤተሰቦቿም የሞራል ካሳ ብር 2,500.00 (ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር) ቅጣት ይከፍላል፣
ሐ) በዚህ ጉዳይ የተባበሩ፣የደበቁ፣መጠለያ የሰጡና ያስታረቁ ግለሰቦች እያንዳንዳቸው ብር 800.00 (ስምንት መቶ ብር) ይቀጣል፣
መ) የውርስ ጋብቻ፣የሴት ልጅ ግርዛት፣እንጥል መቁረጥ፣ጥፍር መቅፈፍ፣ግግ መንቀል፣ጐሮሮ ማስቧጠጥ፣ንቅሳት፣የአይን ቆብ መብጣት፣አላስፈላጊና ለኤች.አይ.ቪ. (ኤድስ) በሽታ መተላለፊያና መንስዔ ስለሆኑ ይህንን ተላልፎ የተገኘ በሕግ የመጠየቁ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ ብር 1,200.00 (አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር) ይቀጣል፣
አንቀፅ 18፡- ቢተን ዎውጣ (ጐጆ መውጣት)፡- ከወላጆቻቸው ይኖሩ የነበሩ ወንድና ሴት በክስታኔ ቤተ ጉራጌ የጋብቻ ደንብና ስርዓት በሚከተሉት እምነት መሠረት ተጋብተው ጐጆ ሲወጡ ወላጆች ወይም ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ቢተን (ጐጆ መውጫ) መሥጠት የተለመደ ሲሆን ይህም መቀጠል አለበት፡፡ በተለይም የወንዱ ወላጆች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ልጆቻቸው ቢተን (ጐጆ) እንዲወጡና እንዲቋቋሙ የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡
አንቀጽ 19 ብሸ (ለቅሶ፣ሀዘን)
፡- በክስታኔ ቤተ ጉራጌ ዕድሜን፣ፆታን፣ማዕረግን፣ታሪክን ወዘተ. መሠረት ያደረገ የለቅሶ ስርዓት እንዳለው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ይህ ስነስርዓት እየተጠበቀ ባለመሆኑ፡-
ሀ) የቁም ብሽ፡- እንደሟቹ የማህበራዊ አገልግሎትና ታዋቂነት ሁኔታ የሚፈፀም ስለሆነ ይህንኑ ሽማግሌዎችን ለመጠየቅ የነበረው ስርዓት ተጠብቆ መቆየት አለበት፣
ለ) በለቅሶ ወቅት ለሃዘን መስተንግዶ ተብሎ የሚወጣው ወጪ መጠነኛና አቅምን ያገናዘበ መሆን አለበት፣
ሐ) ለጉራና ሃብት የሌላቸውን ሰዎች ዝቅ አድርጐ ለማሳየት የሚደረግ አላስፈላጊ ወጪ መቀጠል የለበትም፤መስተንግዶውም ለሁሉም እኩል መሆን አለበት፣
መ) የለቅሶና ተዝካር ተፈፃሚነት፡- በጐርደና ሤራ የተካተቱት የለቅሶና የተዝካር ደንቦች በክስታኔ ጉራጌ ተወላጆች ሁሉ መከበር አለባቸው፣
ሠ) እሳሪየ፡- ከቀብር በኋላ የሟች ቤተሰብ ወይም ልጆች ሟቹን መንከባከባቸውን ወይም አለመንከባከባቸው የቀበረው ለቀስተኛ ተሰብሰቦ በእሳሪየ ዳኞች አማካኝነት የሟች ጐረቤት የሆኑትን ሟቹን መንከባከባቸው ወይም አለመንከባከባቸው በመጠየቅ ጐረቤቶቹ መንከባከባቸውን ከመሰከሩላቸው እንዲመረቁና ቅቤ እንዲቀቡ በማድረግ ይመረቃሉ፤ በተጨማሪም አለመንከባከባቸው ከተመሰከረባቸው ቤተሰቦቹ ወይም ልጆቹ ከለቅሶ ፊታቸውን እንዲያዞሩና ወደ ቤታቸው ብቻቸውን እንዲመለሱ በማድረግ፣በመውቀስ፣በማውገዝ ዳኞቹና ሕዝቡ ያሰናብታቸዋል፤ወደ ሟቹ ቤትም አይመለሱም እንዲያፍሩም ይደረጋሉ፡፡ ይህ ባሕል ወላጆች እንዲጦሩ እና ልጆችም ወላጆቻቸውን እንዲንከባከቡ የሚያደርግ በመሆኑ መቀጠል አለበት፣
ረ) የእሳሪየ ዳኞች፡- በየአገሩ በጐሳቸው የተመረጡ በመሆናቸው ይህን ሕዝቡ የጣለባቸውን ኃላፊነት በማጠናከር እንዲቀጥሉበትና ሕዝቡም ከበሬታ ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑን አውቀው በለቅሶ ወቅት ራሳቸው ይህንን ጥሩ ባሕል እንዲቀጥል ማድረግ አለባቸው፣
አንቀፅ 20፡- አካባቢን መንከባከብ፡-
ሀ) ባሕርዛፍ ብዙ ውሃ ስለሚያስፈልገውና ሥሩም ረጅም ቦታ ሄዶ ውሃ ስለሚስብ ከእንሰትና ከሌሎችም ሰብሎች ራቅ ብሎ መተከል አለበት፣
ለ) በምንጭ ውሃ አጠገብና በሁለት ባለይዞታዎች ወሰን ላይ ባሕርዛፍ መተከል የለበትም፣
ሐ) የእንሰት፣የጐመንና ሌሎችም የምግብ ሰብሎችን ቦታ በማያሻማና ዕድገታቸውን በማይጐዳ ወይም ደረጃቸውን ዝቅ በማያደርግ ሁኔታ ብቻ መተከል አለባቸው፣
መ) እንሰት በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥና በውጭ አገር በከፍተኛ ደረጃ ታዋቃና ተፈላጊ እየሆኑ የመጡት አጥሚጥ (የቆጮና የቡላ) ምርቶች ከምንጫቸው ተዳክሞ ስለሚታይና አሳሳቢም ስለሆነ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፣
ሠ) እንሰት የተፈጥሮ ችግሮችን መቋቋም የሚችል በመሆኑና ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ በብዛትና በጥራት እንዲመረት የሚመለከታቸው በሙሉ ያልተቆጠበ ጥረት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለባቸው፡፡ አርሶ አደሩም እውነታውን ተረድቶ ምርቱን ሊያጐለብት ይገባል፣
ረ) ምሁራንም የእንሰት ዕድገትን የሚያፋጥኑ፣እንዲሁም የሚያጠቁትን በሽታዎች ለመከላከልና ብሎም ለማጥፋት የሚያስችል ጥናቶችን በማድረግና የጥናት ውጤቶችንም ወደ ታች በማውረድ ሁሉም ተባብሮ የእንሰት ምርት ዕድገት እንዲጐለብት ማድረግ ይጠበቅበታል፣
አንቀፅ 21፡- ማሕበራዊ መተጋገዞች፡-
1. ዕድርና እቁብ፡-
ዕድርና እቁብ በተለይ በጉራጌ ክልል ለልማት ሥራዎች በድጋፍ ሰጪነቱ ከፍተኛ ሚና የተጫወተና በመጫወትም ላይ የሚገኝ ሲሆን የጉራጌ ልዩ መታወቂያ ስለሆነ ሁለቱም ከዚህ በበለጠ የልማት ማንቀሳቀሻ እና መረዳጃ ሞተሮች መሆን እንዲችሉ ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማደራጀት መቀጠል አለበት፣
2. ዎቻ፡-
ሀ) ዎቻ ከብት የተሰጠው ሰው ላሚቷን በመንከባከብ ስትወልድ ወተቷን በመጠቀም የማርባት ዘዴ ነው፣
ለ) ዎቻ ሰጪው ተቸግሮ ወይም በሌላ ምክንያት ዎቻ የተሰጠው ሰው በአንድ ዙር ወተቷን ሳይጠቀም የሚወስድበት ከሆነ ለተወሰደበት ሰው ብር 1,000.00 (አንድ ሺህ ብር) ካሳ ከፍሎ ላሚቷን መውሰድ ይችላል፣
ሐ) ዎቻ የተሰጠው ሰው በአንድ ዙር ወተቷ ከተጠቀመ በኋላ ባለዎቻው ላሚቷን ለመውሰድ ጠይቆ አልሰጥም ካለ ዎቻ ሰጪውን በማጉላላቱ ብር 300.00 (ሦስት መቶ ብር) ተቀጥቶ ላሚቷን እንዲመልስ፣
መ) ለግርፍ የተሰጠ ወይፈን ግርፍ ሰጪው ወይፈኑን ለመመለስ ብር 1,000.00 (አንድ ሺህ ብር) ከፍሎ መመለስ ይችላል፣
3. ቆት፡-
ቆት ከዎቻ ስርዓት የተለየ ስለሆነ በሁለቱ ተዋዋዮች መካከል በሚደረግ ስምምነት መሠረት መፈፀም አለበት፡፡
4. ጥጃ፡-
ከአምስት ወንዶች በላይ በመደራጀት በየተራ ድግስ እየተደገሰ የእንሰትም ሆነ ሌሎችም ሥራዎች በጋራ ተባብሮ በአንድ ቀን ሥራን የማጠናቀቂያ ዘዴ ነው፡፡
5. ግቦ፡-
ከአምስት ወንዶች (ሴቶች) በታች በመደራጀት በየተራ በመግባባት አብሮ የሚሰሩበት የሥራ ሥልት ነው፡፡
6. ጂጊ፡-
አንድ አቅመ ደካማ የሆነ ወይም ባለሃብት የአካባቢውን ሕብረተሰብ የጉልበት ሥራ እንዲረዳ በመለመን የእንሰት ሥራም ይሁን ሌሎችም ሥራዎች ድግስ በመደገስ እንዲሰራለት የሚያደርግበት ዘዴ ነው፡፡
7. ውሳቻ፡-
ከአምስት ሴቶች በላይ በመደራጀት በየተራ ድግስ እየተደገሰ የእንሰትም ሆነ ሌሎችም ሥራዎች በጋራ ተባብሮ በአንድ ቀን ሥራን የማጠናቀቂያ ዘዴ ነው፡፡
8. ውጆ፡-
እስከ አምስት ሴቶች በመደራጀት የወተትና የቅቤ እቁብ (ማህበር) የመረዳጃ ዘዴ ነው፡፡
አንቀፅ 22፡- አልኮልና ሌሎች ጐጂ እፆች፡-
1. የአልኮል መጠጥ፡- አልኮል በተለይ አረቄ በጉራጌ ሕብረተሰብ ላይ የሥራ ባሕሉን በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰና በጤናውም ላይ ጉዳት እያስከተለ በመምጣቱ ጐጂ መሆኑን በጐርደና ሤራ ለሁሉም ተወላጅ ጐጂነቱን በማስረዳት ከመጠጣት እንዲቆጠብ ግንዛቤ መፍጠር፡፡
ሀ) እርሻ በሚታረስበት ጊዜና ቦታ፣
ለ) ሽምግልናና ዳኝነት በሚታይበት ጊዜና ቦታ፣
ሐ) ቤት ጊዜና ቦታ፣
መ) በቀብርና ለቅሶ በተቀመጡበት ቦታ፣
ሠ) የጋብቻ ስርዓት በሚፈፀምበት ቦታ፣
ረ) በወንዶችና በሴቶች የደቦ ሥራ ቦታ…. ወዘተ.
ከላይ በተዘረዘሩትና በሌሎችም ማሕበራዊ ግንኙነቶች ቦታ አረቄ ከመጠን በላይ ማቅረብና መጠጣት እጅግ በጣም ጐጂ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፤እንዲሁም ይህን በሚፈፅሙ ላይ የአካባቢ ሽማግሌዎች ማውገዝ አለባቸው፡፡
2. ጫት መብላት (መቃም)፡- በአሁን ደረጃ በከተሞች አካባቢ በወጣቱና በአንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ እየተለመደ የመጣ በመሆኑ እንደአረቄ ሁሉ በጉራጌ ብሄረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ሊታሰብበትና ሊታረም እንደሚገባ በምክር ቤቶች ሁሉ ምክር እንዲሰጥበት ሆኖ ከላይ በተራ ቁጥር 1 ከሀ-ረ በተጠቀሱት ቦታዎችና በት/ቤቶች እንዲሁም በሌሎች ተቋማት ውስጥ መጠቀም የተከለከለ ሲሆን ይህን በሚፈፅሙ ላይ ክትትል በማድረግ የአካባቢ ሽማግሌዎች ሊያወግዙት ይገባል፡፡
3. ሲጃራና ሌሎች ጐጂ እፆች፡-
ሀ) ሲጃራ ማጨስ ለጤና ጠንቅ መሆኑ ታውቆ ህብረተሰቡ ሲጋራ ባለማጨስ ጤንነቱን እንዲጠብቅ ብርቱ ማሳሰቢያ መስጠት፣
ለ) በስብሰባ ቦታ፣በት/ቤቶች አካባቢ፣በመንግሥት መ/ቤቶች አካባቢ ሲጃራ ማጨስ በፍፁም የተከለከለ መሆኑን፣
ሐ) እንደ ሃሺሽ፣ሺሻና የመሳሰሉት ጐጂ እፆች በማናቸውም ጊዜና ቦታ መጠቀም የተከለከለ በመሆኑ ህብረተሰቡ እየተከታተለ ማህበራዊ እርምጃ እንዲወስድ ተወስኗል፣
አንቀፅ 23፡- የቤት አሰራር፣የጐርደና ሞጨ፣የድንበር እማየ፡-
1. የክስታኔ ቤተ ጉራጌ ቤት አሰራር፡-
የክስታኔ ቤት አሰራር ከጥንት ጀምሮ ከውጪም ሆነ ከውስጥ የሚገነባው ግንባታ የቤተሰብን ድርሻ ያገናዘበ ወይንም የሚወክል በመሆኑ ይህንኑ እንዲቀጥል ሆኖ የነፋስና የብርሃን መስኮት እንዲኖረውና ሌሎችም ጠቃሚ ማሻሻያዎች ተደርገውበት ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ ማሳወቅ፤ማስገንዘብ፡፡
2. የጐርደና ሞጨ፡-
ሀ) በክስታኔ ቤተ ጉራጌ የጐርደና ሞጨ (መንገድ) አከላለልና አጠባበቅ ሤራ (ደንብ) አለው፤በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙ ቦታ ደንቡ እየተጣሰ በመንገዱ ላይ አጥር በማጠር፣ቤት በመሥራት፣አትክልትና ዛፍ በመትከል አየጠፋ ስለሆነ ይህ አድራጐት ተገቢ ስላልሆነ የአካባቢው ሽማግሌዎች ጥንት የነበረውን የጐርደና ሞጨ በመለየትና በማስጠበቅ ማቆየት አስፈላጊ ነው፣
ለ) የጐርደና ሞጨ (መንገድ) አገልግሎት የጋራ እንደመሆኑ መጠን የሚወሰነው በተጠቃሚው ጠቅላላ ሕዝብ እንጂ በአንድ ተገልጋይ ብቻ ስላልሆነ አገሩ ወይም ቀበሌው በሽማግሌዎች በመታገዝ ጥንት የነበረውን የጐርደና ሞጨ (መንገድ) እንዲከበር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፣
ሐ) የመንደር ወይም የቤተክርስቲያን መንገዶች የሕዝብ መተላለፊያ በመሆናቸው በአንዳንድ አካባቢ እየተዘጉ ስለሆነ በነበረው ባሕል መሠረት መንገዶቹ ሳይዘጉ ሕዝብ እንዲገለገልባቸው እንዲደረግ የአካባቢው ሕብረተሰብ መተባበር አለበት፣
3. የድንበር እማየ (ድንጋይ)፡-
የሁለት ይዞታዎችን መሬት፣የጐርደና ሞጨ እንዲሁም ከሌሎች ይዞታዎች የሚለየው በድንበር ድንጋይ በመሆኑ ይህንን ድንበር ማክበርና ማስከበር ግዴታ ሲሆን ድንበሩን በቀንም ሆነ በሌሊት የነቀለ ሰው ብር 300.00 (ሦስት መቶ ብር) ቅጣት ከፍሎ የድንበሩን ድንጋይ ወደነበረበት የመመለስ ግዴታ አለበት፤አፈፃፀሙም አለመተማመን ከፈጠረ በ5 (አምስት) ሽማግሌዎች አማካኝነት ለፌ በመጥራት ወይም መሃላ በመፈፀም ይተገበራል፡፡
አንቀፅ 24፡- የባሕል ቅርሶችን የመጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት፡-
ሀ) የጉራጌ ባሕል ቅርስ የሆኑ ዕቃዎች በመጥፋት ላይ በመሆናቸው ዕቃዎቹን ሁሉ የሚያካትት ሙዚየም መሥራት ጊዜ፣ሃብትና ድርጅት የሚጠይቅ በመሆኑ ሕዝቡ ብርቱ ጥረት በማድረግ ቅርሶቹን የመጠበቅና የመንከባከብ እንዲሁም የማስጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት አለበት፣
ለ) ህብረተሰቡ በየአካባቢው ያሉ ታሪካዊ ቦታዎችን፣የተፈጥሮ መስህቦችን፣ትክል ድንጋዮችን፣ የሃይማኖት ቦታዎችን፣የመናፈሻ ቦታዎችና የጐርደና ሸንጐ መሰብሰቢያ ቦታዎች የመጠበቅና የማደራጀት ግዴታና ኃላፊነት አለበት፣
ሐ) ያሉት ዋና ዋና የቅርስ ዕቃዎች በእንክብካብ እንዲጠበቁ ሆኖ የጠፉትንም በአይነታቸው አስመስሎ በመስራት ቢሸጡ ገቢ ስለሚያስገኙ እንዲሰሩ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፣
አንቀፅ 25፡- ባሕላዊ ህክምና፣ስፖርትና ኪነት
1. ባሕላዊ ህክምና፡-
ሀ) ህብረተሰቡ በባሕላዊ ህክምናዎች ከመጠቀሙ በፊት በተቻለ መጠን በዘመናዊ ህክምና እንዲጠቀም ማበረታታት ይገባል፣
ለ) የባሕል ህክምና ሰጪዎች፣መርፌ ወጊዎች በሚያክሙበት ጊዜ መጠጥ እንዳይወስዱ ጥንቃቄ ከማድረግ ባሻገር የአጥንት ስብራት፣የወለምታና ሌሎችም ህክምና የሚሰጡ እውቅ የልምድ ባለሙያዎች፣አዋላጆች አሰራራቸውና መድሃኒት አሰጣጣቸው በህብረተሰቡ ጤና ላይ አደጋ እንዳያስከትል የጤና ትምህርት እንዲቀስሙና አገልግሎታቸውን በጥንቃቄ እንዲሰጡ እንዲደረግ፣
2. ስፖርት፡-
ስፖርት በጉራጌ ባሕል ውስጥ ሊበረታቱና ሊጠበቁ የሚገባቸው ስፖርቶች ብዙ ቢሆኑም ያለባቸውን ድክመት (ጉዳት) እንዳያስከትሉ ታርመው በተሻሻለ ሁኔታ መቀጠል አለባቸው፤እነርሱም አንቃት (ሩር)፣የአጋት ዝላለ፣ሰዲቃ፣ሰባ፣የፈረስ ጮታ፣መጆ አራጆ፣ ዎቅለ፣ቀጨሌ፣የምድር ዝላለና ግጂላ ሌሎችም እየተጠኑ ግልጋሎት ላይ የሚውሉበት ሁኔታ እንዲመቻች፡፡
3. ኪነጥበብና ኪነት፡-
ሀ) በክስታኔ ቤተ ጉራጌ ባሕል ደርስ (ዘፈን)፣ውንቂትና ዎግ ሌሎችም ማህበራዊ ከበሬታዎች እንዲዳብሩ በአንፃሩም ማህበራዊ ነውሮች እንዲከስሙ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ፣ልጆችም ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩን እንዲጦሩ የልማት ሥራዎቸ እንዲጠናከሩ በጥናት በተደገፈ ሁኔታ እንዲዳብር መደረግ አለበት፣
ለ) ልዩ ልዩ ባሕላዊ ጨዋታዎችና ኪነጥበባት ተሰብስበውና ተጠንተው ሕይወት ሊዘሩ በሚችሉበት ሁኔታ መቀረፅ አለባቸው፣
አንቀፅ 26፡- የጐርደና ሸንጐ መሰብሰቢያ ጊዜ፡-
ሀ) አጠቃላይ የጐርደና ሸንጐ ምክር ቤት በምክር ቤቱ ደረጃ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ሳያጋጥሙ ሽማግሌዎች ተጠርተው በዓመት 3 (ሦስት) ጊዜ እንዲሆንና አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥም በጥሪ መሠረት መሰብሰብ ይቻላል፣
ለ) በስብሰባ ወቅት ሰዓት ማክበር ተገቢ በመሆኑ የዓለማችን ስልጣኔ ከደረሰበት ደረጃ አኳያ ጊዜ ፍፁም ወርቅ ስለሆነ ሁሉም የሸንጐ አባላት ሰዓት አክብረው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፣
ሐ) ሸንጐ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት መረጃዎችን በአግባቡ ማቅረብና ማብላላት፣ የሃሳብ ሙሉ በሙሉ ማንሸራሸር ተገቢ ሲሆን የማያስፈልጉ ድግግሞሾችን በማስቀረትና ጊዜ በመቆጠብ ከመሰላቸት የፀዳ አቋም ያለው ውሳኔ ማስገኘቱ የጋራ ኃላፊነት በመሆኑ ሁሉም የሸንጐ አባል ሁኔታዎችን ሊያከብር ይገባል፣
መ) የስብሰባው ውጤት በሰነድነት በመመዝገብ በተለይም የሚተላለፉ ውሳኔዎች ወደታችኛው አካል ለማውረድና ለታሪክ መዘክርነት፣ለአርአያነት፣ሸንጐውን ለማዳበርና ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚኖራቸው በቋሚ መዝገብ እየተመዘገቡና በትክክል ለመስፈራቸው ቢያንስ በሽማግሌዎች፣በሰብሳቢና በፀሐፊ ፊርማ እየተረጋገጠ በሰነድነት መያዝ አለባቸው፣
አንቀፅ 27፡- ከቅጣት የሚገኝ ገቢ አጠቃቀም፡-
ሀ) በጐርደና ሸንጐ በየደረጃው የሸንጐውን ሤራ (ደንብ) ከጣሱ ተወላጆች የሚሰበሰበው የቅጣት ገንዘብና ሸንጐው በእርዳታና በተለያዩ ሁኔታዎች የሚያገኘውን ገቢ (ገንዘብ) ለአካባቢው ልማት ሥራ መዋል አለበት፣
ለ) የገቢና ወጪ ሁኔታዎች በዝርዝር በሕጋዊ ደረሰኝ ከተመዘገቡ በኋላ ሸንጐው ለሚወስናቸው ውሳኔዎች ማስፈፀሚያ ጭምር ማዋል ይገባል፣
አንቀፅ 28፡- የጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) ስለማሻሻል፡-
ይህ የተሻሻለው የጐርደና ሸንጐ በሙሉም ሆነ በከፊል የሚሻሻሉ ወይም ሌሎች የሚጨመሩ ጉዳዮች ሲኖሩት ከየአገሩ ሕዝብ በእኩል ቁጥር በሚወከል የጐርደና ሸንጐ ጠቅላላ ምክር ቤት ሊሻሻል ይችላል፡፡
አንቀፅ 29፡- የጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) የሚፀናበት ጊዜ፡-
ይህ የጐርደና ሸንጐ መተዳደሪያ ሤራ (ደንብ) ከ ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡