አ/አ ዮንቨርስቲ የሚገኘው ትክል ድንጋይ ጉማጅ

 

በዓለም ቅርስ ዝርዝር መሠረት እ.ኤ.አ በ2012 በዓለም 936 የዓለም ቅርሶች የተመዘገቡ ሲሆን 725 ባህላዊ 183 ተፈጥሯዊ እና 28 ጥምር ባህላዊ እና የተፈጥሮ ቅርሶች 113 ሃገሮች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ቅርሶች ከሃገር ዉጪ ሌላውን ዓለም በማስደነቅ የዓለም ህዝብ ንብረቶች እንዲሆኑ በዩኔስኮ ምዝገባ የተጀመረው እ.ኤ.አ 1978 ነበር፡፡ 43 ቅርሶችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ሃገር አውሮፖዊቷ ጣሊያን ናት፡፡ ሃገራችን ኢትዮጵያ 9 ቅርሶችን በዩኔሰኮ ዓለም አቀፍ ቅርሰነት አስመዝግባለች እነዚህም፡- የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስያቲያን በ1978 ዓ.ም የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፖርክ በ1978 ዓ.ም ፣ የፋሲል ግንብ በ1979 ዓ.ም የአክሱም ሃውልት በ1980 ፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ 1980ዓ.ም የታችኛው ኦሞ ሸለቆ በ1980 ዓ.ም፣ ጢያ ትክል ድንጋይ 1980 ዓ.ም ፣ የጀጎል ግንብ 2006 ዓ.ም ፣ ኮንሶ ባህላዊ መልከዓ ምድር 2011 ዓ.ም የመሰቀል በአል አከባበር፤የጥምቀት በአል አከባበበር ስነ ስርአት፤የኢሬቻ በአል አከባበርና የፊቼ ጨምበለላ በአል አከባበር ስነስርአት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም የቅርስ መዝገብ ዩኔስኮ ከተመዘገቡላት  የተለያዩ ቅርሶች መካከል የጢያ ትክል ድንጋዮች አንዱ ነው፡፡ የጢያ ትክል ድንጋዮች በደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ውስጥ ከአዲስ አበባ 86 ኪ.ሎ ሜትር እንዲሁም ከመልካ ቁንጥሬ 40 ኪ.ሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ጢያ ትክል ድንጋዮች በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው እ.ኤ.አ በ1980 ሲሆን የተመዘገበበት ምክንያት 3 ዋና ዋና ምክንያቶች አሉት እነሱም፡-

  1. የጥንት የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት መሆኑ
  2. የጥንት የሰው ልጅ የመኖሪያ አካባቢ መሆኑና
  3. የጥንት የፈጠራ ውጤት ሆኖ ለዛሬው ትውልድ ፈር ቀዳጅ መሆኑ ነው፡፡

በጢያ ምድር ባረፈው የቀረሶቹ ክልል ከ12ኛው እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የተተከሉ መሆናቸው የሚነገርላቸው ከ700 እስከ 900 ዓመት ዕድሜ ይሆናቸዋል ተብለው የሚገመቱ 41 ትክል ድንጋዮች ይገኛሉ፡፡

ከነዚህም መካከል 5 ሜትር ርዝማኔ ያለው ትክል ድንጋይ ረጅሙ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የዚህ ጉማጅ በአዲስ አበባ ስድሰት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ጊቢ ውሰጥ ይገኛል፡፡

የጎራዴ ምስል ያለው ጢያ ትክል ድንጋይ

ትክል ድንጋዩቹ ርዝመታቸው የተለያየ ሲሆን በቁመቱ ትንሽ የሚባለው ደግሞ 1 ሜትር ነው፡፡

ድንጋዩቹ የቆሙበት ምክንያት ለሟቾቹ የቀብር ሃውልት እንዲሆኑ ታስቦ ሲሆን የተቀበሩትም ሰዎች በአካባቢያቸው የጀግንነት ተግባር ፈጽመው ያለፋ መሆኑ በተመራማሪዎች ተረጋግጧል፡፡

በነዚህ ታሪካዊ ድንጋዩች ላይ የተለያየ ምስል ተቀርፆባቸው ይታያል፡፡ ሮጀር ጄሶም በተባለ ፈረንሳዊ ዜጋና ዶክተር ካሳዬ በጋሻው በተሰኙ አረኪዮሎጂስቶች እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም በቁፋሮ የተደረገው ምርምር እንዳሳየው ትክል ድንጋዩቹ ያረፋበት ስፍራ የቀብር ቦታ መሆኑን የሚያስረዳ መረጀ ተገኝቷል፡፡ ተመራማሪዎቹ ትክል ድንጋዩቹ ባረፋበት በ264 ካ.ሜ ክልል ወስጥ ቁፋሮ አድርገው 52 አጽሞች አግኝተዋል፡፡ የተቀበሩት ሰዎች ከ18 እስከ 30 የእድሜ ክልል ውስጥ መሆናቸው በአጥኚዎች ተረጋግጧል፡፡ አጽሞቹ እንደሚያሳዩት በአንድ ቀብር ውስጥ ከሁለት በላይ ግለሰቦች የተቀበሩበት የህብረት መቃብር መሆኑ ሲረጋገጥ ፣ አንድ የቀብር ስፍራ ብቻ አንድ ሰው በነጠላ የተቀበረበት ተገኝቷል፡፡

በቀብር ሥርዓቱ ሞቾቹ ቁጢጥ/ቁጭ/ ብለው መቀበራቸው ሲታወቅ አንዱ ቀብር ብቻ ተንጋሎ የተቀበረ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ እንደ አርኪኦሎጂስቶቹ ትንታኔ ቁጢጥ ብለው የተቀበሩት 51 አጽሞች የክርስትና ሐይማኖት ወደ አካባቢው ከመግባቱ በፊት የተከናወኑ ሲሆን ተንጋሎ የተቀበረው አጽም ደግሞ ክርስትና ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ የተፈፀመ መሆኑን ያመለክታል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በተመራማሪዎቹ ቁፋሮ የሰዎቹ አጽም በ2 ሜትር ጥልቀት ላይ የተገኘ ሲሆን ከአጽሞቹ በ 0.5 ሜትር ርቀት ከፊትና በተመሳሳይ ርቀት ላይ ከበስተጀርባቸው የተለያዩ መዋቢያ ጌጣ ጌጦች ተገኝተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የአንገት ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ የእጅ አንባር፣ ዶቃ፣ ጨሌ፣ ባልጩት እና የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶች አብረው ተቀብረው ተገኝተዋል፡፡

በክትል ድንጋዮቹ ላይ የተቀረፀው ምስል ቁጥር እንደየ ድንጋዩ ሲለያይ በአንድ ትክል ድንጋይ ከ1 እስከ 19 የሳንጃ ምስል መቀረፁን የሟቾቹ የጀግንነታቸው ወይም የገደሉት የዱር እንስሳት ብዛት ለመግለጽ እንደተጠቀሙበት መላ ምት ተሰጥቷል፡፡

የክብ ጡት ምስል የተቀረፀባቸው ትክል ድንጋዩች ደግሞ ቀርፁ አነስተኛ ሆኖ የሚታየው ሟቹ ተባዕት መሆኑን ሲገልጽ የክብ መጠኑ የሚተልቅበት የእንስት ፆታን ለማመልከት ነው ተብሏል፡፡

በድንጋዩቹ ላይ ከተቀረፁት ምስሎች መካከል የባህላዊ መንተራሻ ቅርጽና የእንሰት ተክል ምስል ደግሞ ግለሰቦቹ በኖሩበት ጊዜ ይገለገሉበትና ይመገቡበት የነበረውንና የወቅቱ ባህላዊ መገልገያ ቁሶች ምን እንደነበሩ ለማሳየት እንደሆነ የአርኪኦሎጂሰቶች ትንታኔ ያስረዳል፡፡

በጢያና አካባቢዋ ከ6 የማያንሱ የትክል ድጋይ ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡

ከነዚህ መካከል

  • የሰው ምስል የሚያሳይ የተቀረፀባቸው /Antromorfic Stelae/

 

  • የሳንጃ ቅርጽ የተቀረፀባቸው/Sword Stelae/

 

  • ምስሎች የተቀረፀባቸው ትክል ድንጋዮች /Figerative Stelae/

 

  • የወንድ ብልት ቅርጽ ያለው /Phallic Stelae/

 

  • የፊት ማስዋቢያ ምልክት የሚያሳይ ምስል የተቀረፀባቸው /Facial Ritual Mark Stelae/

 

  • የከበሮ ምስል ወይም የነጋሪት ቅርጽ ያለው  /Drum Stelae/ በመባል ይመደባሉ፡፡

በጢያ መካነ ቅርስ ላይ በብዛት የሚገኙ ትክል ድንጋዩች ጎራዴ መሰል ቅርጽ ያላቸው ሲሆኑ ቁጥራቸው 36 እንደሆነ ከአስርት ዓመታት በፊት በመካነ ቅርሱ ላይ ጥናት ያካሄዱ አርኪዮሎጂስቶች ጽፈዋል፡፡

ከትክል ድንጎዩቹ መካከል 41 በሚሆኑት ላይ የተለያየ ቅርጽ ያላቸው ምስሎች አሉባቸው፡፡ ምስሎቹ የተቀረፁት በአንደኛው የድንጋዩ ፊት በኩል ነው፡፡ በስፋት ድንጋዩቹ ላይ ከተቀረፁት ምስሎች መካከል የጎራዴ ቅርጽ፣ ክብ ወይም ዲስክ ምስል ቅርጽ የእንሰት ተክል የመሰለ ቅርጽና የጎድን አጥንት የሚመስል ቅርጽ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

እነዚህ ትክል ድንጋዩች ቀደም ሲል ተፈልፍለው ወይም ተጠርበው የመጡት በአካባቢው ከሚገኘው አለልቱ ከተባለው ወንዝ ስር ሲሆን ከትክል ድንጋዩቹ በግምት 1 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም የተረጋገጠው አርኪኦሎጂስቶች በስፍራው ባደረጉት ጥናትና በተገኙ ተመሳሳይ የትክል ድንጋይ ቅርፆች ከዚያ ተጠርቦ ለመምጣታቸው ማሣያ ሆኗል፡፡

እያንዳንዱ ትክል ድንጋይ ለመያዣነት የሚያገለልሉ 2 አና 3 ቀዳዳዎች አሉት፡፡ ይህም ከአለልቱ ወንዝ ተጠርቦ እየተጎተተ እስከ ተተከለበት ስፍራ ድረስ የመጣበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡