የጐርደና ሸንጐ የባሕል መተዳደሪያ ሤራ

ሶዶ ወረዳ በደቡብ ብሄርብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት በጉራጌ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ነው፤በውስጡም የተለያዩ ብሔረሰቦች በመከባበርና በመግባባት አብረው ይኖራሉ፡፡
በወረዳችን የሚኖረው ሕብረተሰብ የሚተዳደረው በክልሉ ሕገ-መንግስት መሠረት ቢሆንም የጉራጌ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ከአያት ቅድመ አያቱ የወረሳቸው ቀደም ባሉ ዘመናት መንግስት ሳይመሰረትና ሕገ-መንግሥት ሳይቀረፅ ከረጅም ዘመናት በፊት ሕዝቡ ሲተዳደርባቸው ቆይተው እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቁ የራሱ የሆነ ጠንካራ ባሕላዊ እሴቶች ያሉት እና ከአያት ቅድመ አያቱ የወረሳቸው በርካታ ባሕሎች አሉት፡፡ ጠንካራ ባሕላዊ እሴቶች ለመልካም አስተዳደር መጐልበት ለተሻለ ልማትና ለተሻለ ሰላምና ፀጥታ እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፆኦ እያበረከተ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ደግሞ በልማት፣በመልካም አስተዳደር፣በሰላምና ፀጥታ በሕዝቡ ጤንነት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ስለሆነም የተፋጠነና ዘላቂ ልማት ለማምጣት አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለመፍጠር መልካም የሆኑ ባሕሎቹን ጠብቆ ለማቆየት እንዲሁም ጐጂ ልማዳዊ ድርጊትን ለማስቆም የጐርደና ባሕል ሽማግሌዎች ማጠናከርና ደንብ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህ መሠረት የወረዳው ባሕል ቱሪዝምና መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ለጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) ጠብቆ ለማቆየት ከየቀበሌው ሁለት ሁለት ሽማግሌዎችን በማስመረጥ በወረዳ ደረጃ በማወያየትና በተደረሰበት ደረጃ በድጋሚ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) ላይ በማወያየት የሚሻሻለውን በማሻሻልና በማረምና የሀገሪቱ ህገ መንግሰት በማይጻረር መልኩ ታይቶ የተደረሰበት ደረጃ ወደታችኛው አካል ለማድረስና በሰነድነት ለማስቀመጥ እንዲቻል ይህ የጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡

በመሆኑም ይህንን ደንብ ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉም ወገኖች ያላሰለሰ ጥረት ስለሚጠይቅ ለደንቡ ተፈፃሚነት ሁሉም የወረዳው ሕዝብና የብሄረሰቡ ተወላጆች በያሉበት ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡

አንቀፅ 1፡- የጐርደና ሤራ፡- የክስታኔ ቤተ ጉራጌ ባሕላዊ መተዳደሪያ ደንብ ሲሆን በመንደር፣ በቀበሌ፣ በሃገር ደረጃ መሠራታዊ፣ማህበራዊ ግንኙነቶችና ትስስሮችን ለማጠናከር የሚወጣ ደንብ ነው፡፡
አንቀፅ 2፡- የጐርደና ሸንጐ ሤራ አላማዎች፡-
ሀ) የክስታኔ ጉራጌ ሕዝብ ባሕል፣ታሪክና ቋንቋ ለማሳደግና ለመንከባከብ፣
ለ) በአጐራባች ወረዳዎች መካከል የሚፈጠር ግጭቶችን ለመፍታት፣
ሐ) የእድገትና የመልካም አስተዳደር ፕሮጀክቶች በአግባቡ እንዲፈፀሙ ለመደገፍ፣
መ) በወረዳው ውስጥ ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሕግ የማቅረብ እንቅስቃሴን ለማቀናጀት፣
ሠ) የጉራጌ ሕዝቦችን አንድነትና ውህደት ለማጠናከር፣
ረ) በጐርደና ሸንጐ የተነደፉ ባሕላዊ ሕጎች በአግባቡ መተግበራቸው ለመከታተል፣
ሰ) በጐርደና ሸንጐ ቀደም ሲል የሚመረጡት ወንዶች ብቻ እንደሆኑ ይታወቃል፤ይህ ተሻሽሎ በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑ አዋቂና ሕብረተሰቡ የሚያምንባቸው ወጣቶችና ሴቶችንም በማሳተፍ እንዲሆን ለማድረግ ይሆናል፡፡
አንቀፅ 3፡- የጐርደና ሤራ አፈፃፀም ሥርዓትና ተዋረድ፡-
ሀ) የጐርደና ሸንጐ፡- የሁሉም አገር ሽማግሌዎች ጠቅላላ ስብሰባ ነው፡፡
ለ) የአገር ሸንጐ፡- በርካታ ሳቡኘቶችን (ቀበሌዎችን) ያካተተ የሚወክል ነው፡፡
ሐ) የጥብ ሸንጐ፡- የአንድ ጐሳ አባላትን በማሳተፍ የሚካሄድ ነው፡፡
መ) ሳቡኘት፡- ከየትኛውም ጐሳ ሃይማኖት፣ሙያ፣የኢኮኖሚ የኑሮ ደረጃ ያሉ የመንደር ነዋሪዎች ያቀፈ ባሕላዊ ተቋም ነው፤የየራሱም ደንብና መመሪያዎቸን ለሃዘንም፣ለደስታም፣ ለሥራም … ወዘተ. ሊኖረው ይችላል፡፡
አንቀፅ 4፡- ለጐርደና ሸንጐ የሚቀርቡ ጉዳዮች፡-
ሀ) በተለያዩ ክፍለ ሕዝቦች (ጐሳዎች) የሚነሱ ግጭቶች፣
ለ) ሸንጐ ውስጥ ለሚያጋጥሙ የትርጉም ችግሮች፣
ሐ) በማንኛውም ደረጃ ይሁን ከየአካባቢው የተሰጡ ባሕላዊ ውሳኔዎች የመጨረሻ ይግባኝ ሰሚ የጐርደና ሸንጐ ምክር ቤት ይሆናል፣
መ) ሸንጐ በማስፈፀም ረገድ ችግሮች ቢኖሩ በዚህ የጐርደና ሤራ መሠረት መፍትሄ እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል፣
አንቀፅ 5፡- የውሳኔ አሰጣጥ፡-
ሀ) ለጐርደና ሸንጐ ምክር ቤት የሚቀርብ ማንኛውም ጉዳይ በጉባዔው በተገኙ አባላት ውሳኔ ያልፋል ወይም ይወሰናል፡፡
ለ) በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በሁለት የተከፈለ የውሳኔ ሃሳብ ከተከሰተ ሰብሳቢው በሚመርጧቸው ሽማግሌዎች አማካይነት ሊወሰን ይችላል፡፡
አንቀፅ 6፡- ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ በይግባኝ ወደሚቀጥለው ደረጃ መጥቶ የሚታይበት ሁኔታ
ሀ) የሥር ዳኝነት ጉዳይ በማቅረብ ብቻ ሳይወሰን ውሳኔ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ የመከታተል፣ከተወሰነ በኋላም የማስፈፀም ሃላፊነት አለበት፡፡
ለ) በዚህ ጉዳይ ዋስ የነበሩ ሰዎች ዋስትናቸው ሳይወርድ እንዳስፈላጊነቱ ጥሪ ሲደረግላቸው በዳኛው አማካኝነት ይቀርባሉ፡፡

አንቀፅ 7፡- የጐርደና ሸንጐ መሰብሰቢያ ቦታዎች

ሀ) የየአገሩ የጐርደና ሸንጐ መሰብሰቢያ የሚሆነው ጥንት የነበረው ቦታ ሆኖ፣ይህም በሸንጐ አባላት ይወሰናል፡፡
ለ) የክስታኔ ጐርደና ሸንጐ ምክር ቤት መሰብሰቢያ ቦታ የሁሉም አገሮች ማዕከል በሆነው በወረዳው ርዕሰ ከተማ ቡኢ ላይ ሆኖ፣እንዳስፈላጊነቱ በሌሎች ከተሞችም ጭምር ይሆናል፡፡
አንቀፅ 8፡- በቋንቋ ስለመጠቀም
ሀ) ቋንቋ ለአንድ ሕዝብ መግባቢያ፣የሃሳብ መለዋወጫ፣የማንነት መገለጫና የባሕሉም ነፀብራቅ ስለሆነ በሸንጐ ወቅት ቢቻል በክስታንኛ ቋንቋ በተለይም የአክብሮት መገለጫ የሆኑትን (አትርፌ ትረፍ፣ሣር ዪበላ ያበነ) በማለት የነበረውን የአባቶች የሸንጐ ስርዓት በተከተለ መልኩ መሆን አለበት፡፡
ለ) አንድ ቋንቋ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችለው እያንዳንዱ ተወላጅ በቋንቋው የመጠቀም ባሕል ሲያዳብር በመሆኑ የክስታኔ ተወላጅ የሆነ በተቻለው መጠን ቋንቋው እንዳይጠፋ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አንቀፅ 9፡- በጐርደና ሤራ ማዕረግ አሰጣጥ
የክስታኔ ቤተ ጉራጌ የጐርደና ሤራን መስርቶ ራሱን በራሱ ያስተዳደር በነበረበት ወቅት አዝማች፣አበጋዝ በማለት የባሕል መሪ ወይም አስተዳዳሪ ለመሆን አንድ ሰው ይህ ማዕረግ የሚሰጠው በአካባቢው በሥነምግባሩ፣በአስታራቂነቱ፣በሥራ ወዳድነቱ፣በኑሮ የተሻለ፣አዋቂና ታዋቂ ለሆነ እንዲሁም ወስላታን የማይወድ ለሠላም የቆመ የተቸገሩትን የሚረዳ መሆን አለበት፡፡ ዛሬም እነዚህ መሪዎች ባሕላዊ አመራር፣የአስተዳደር፣የዳኝነትና የሽምግልና … ወዘተ. አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ ቀደም ሲል መሪዎቹ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሕዝቡ አገልግሎት ያውሉ ስለነበር ሕዝቡም ነፃ የሙያ፣የጉልበት … ወዘተ. አገልግሎት ያበረክትላቸው ነበር፡፡ ይህም አሁንም መቀጠል አለበት፡፡
አንቀፅ 10፡- ወንጀልን ስለመከላከል
ሀ) መገንታ የጦርነት፣ያለመግባባት፣የግጭት፣የጭቅጭቅ፣የወስላታ ጊዜያዊ ማስታገሻ ወይም መግቺያ ማቆሚያ ባሕላዊ የጐርደና ሥርዓት ነው፡፡
ለ) ሁለት ጐሳዎች ቢጋጩ ጉዳዩ ታይቶ እስኪወሰን ሳይነካኩ አንዱ ባንዱ ላይ ፀብ እነዳይጭር ባለበት እንዲቆይ ወይም አባራሪው በዕግድ እንዲቆም የሚደረግበት፣ወይም ተበዳይ በዳይን አግኝቶ ቢያሳድደውና አምልጦ በዕግዱ ወይም በጥብቁ ቦታው ቢደርስ ጉዳት እንዳይደርስበት የሚጠለልበት ወይም የሚከለልበት ባሕላዊ ሥርዓት ነው፡፡
ሐ) መገንታ የተፈጠረው ማንኛውም ግጭት ስምምነት ለመፍጠር፣ምሕረት ለማውረድ የእፎይታ ጊዜ የሚሰጥ ነው፡፡
መ) አፈርሳታ (አውጫጭኝ) ማንኛውም ወንጀለኛ በጥቆማ ለመለየት የሚያስችል ዘዴ ሲሆን የተለየውም ሰው የማያምን ከሆነ ከእናቱና ከአባቱ ወገን ሁለት ሁለት ዘመዶቹ እንዲምሉለት ያቀርባል፤ከልማሉለት ግን ወንጀለኛ መሆኑ ይረጋገጣል፡፡
ሠ) ዋሪሃ (የምሽት ሸንጐ) በየምሽቱ የአቅራቢያ ጐረቤታሞች የሆኑ አዛውንቶች፣ወጣቶች ቤት ውስጥ በየተራ በመሰብሰብ ስለሥራ፣ስለአካባቢ፣ስለአገር ደሕንነት፣ስለታሪክና ባሕል … ወዘተ. የሚመካከሩበት መድረክ ነው፡፡ ይህም መቀጠል አለበት፡፡ ዋሪሃ የአልኮል መጠጫና የአካባቢ ልማትን ለማወክ መሆን የለበትም፡፡
አንቀፅ 11፡- ወንጀል ነክ ድንጋጌዎች

በክስታኔ ቤተ ጉራጌ ባሕል በሰው ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ የተወገዘ ሲሆን በርቼ (ግፍ) እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡
1. የቤት ቃጠሎ
ሀ) በግፍ ቤት ያቃጠለ ሰው በማስረጃ ተረጋግጦበት (ካመነ) ቤቱ ለተቃጠለበት ብር 100,0000.00 (እንድ መቶ ሺህ ብር) ይከፍላል
ለ) የቤቱ ቃጠሎ በስህተት ወይም ባለማወቅ ሲሆን ብር 50,000.00 (ሃምሳ ሺህ ብር) ይከፍላል፡፡
ሐ) የቤቱ ቃጠሎ በስህተት፣ስህተት ያቃጠለ ሰው ለተቃጠለበት ብር 25,000.00 (ሃያ አምስት ሺህ ብር) ይከፍላል፡፡
መ) እንስሳትና የቤት ቁሳቁስ ከተቃጠሉ ዋጋቸው ተገምቶ ከቤቱ በተጨማሪ ይከፍላል፡፡
ሠ) በቃጠሎ የአንድ ወይም ከአንድ ሰው በላይ አካል ቢጐድል በአካል ማጉደል ወንጀል ሤራ መሠረት በያንዳንዱ ሰው በየደረጃው ይጠየቃል፤ይህም ጉዳዩ ከሕግ ጋር ከተያያዘ በዎማኖ ሤራ ተጠይቆ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
2. የሰብል ማቃጠል፣መንቀልና መቁረጥ፡-
ሀ) ማንኛውም ሰው በቂም በቀልና ፍትሕ ተጓደለብኝ ወይም ተበደልኩ በማለት ሰብልን፣አዝርዕትን፣ቡና፣እንሰትና ባሕርዛፍ … ወዘተ. ማቃጠል ወይም መንቀል የተወገዘ ድርጊት ነው
ለ) ይህን ጥፋት የፈፀመ ያጠፋው ሰብል በሽማግሌዎች ተገምቶ ከብር 90,000.00 እስከ 150,000.00 ለባለንብረቱ ይከፍላል፤አልከፍልም ካለ በሕግ ይጠየቃል፡፡
3. ስርቆት፡-
ሀ) የቀንድና የጋማ ከብት የሰረቀ ለጥቆማ የወጣ ወጪ ካለ በተለይ ከፍሎ በመሥረቁ ከብር 150 እስከ 6000 መቀጫ ይከፍላል፡፡
ለ) ከብቶቹንም ለባለንብረቱ ይመልሳል፣መመለስ ካልቻለ በሽማግሌ በተገመተ የገበያ ዋጋቸው ለባለንብረቱ ይከፍላል ወይም መሰል ከብት ይተካል፡፡
ሐ) ሰብል ወይም የእርሻ ውጤቶችን የሰረቀ ከላይ በተራ ቁጥር ሀ የተጠቀሰው መቀጫ ከፍሎ የሰረቀውን እሕልም በነበረበት ሁኔታ ለባለንብረቱ ይመልሳል፡፡
መ) ትምህርት ቤቶች፣የጤና አገልግሎት ተቋማት፣የመሠረታዊ አገልግሎት መስጫ አውታሮች፣የሕዝባዊ ድርጅቶች፣የእምነት ቦታዎች ንብረት የሰረቀ ሌባ የሰረቃቸውን ንብረቶች ሁሉ እንዲመልስ ሆኖ፣መመለስ ካልቻለ በሽማግሌና በባለሙያ ተገምቶ ለባለተቋሙ ይከፍላል፡፡
4. አካል ማጉደል፡- በክስታኔ ቤተ ጉራጌ የሰውን አካል ማጉደል ከበድ ወንጀልና በርቼ ነው፡፡
አይን ማጥፋት፣ጥርስ መስበር፣ጆሮ ማደንቆር፣እጅና እግር መቁረጥ፣አፍንጫ መቁረጥ፣ምላስ መቁረጥ፣ከንፈር መቁረጥ፣ጣት መቁረጥ፣አባላዘር ማበላሸት ሌሎችም ወንጀሎች እንደየጉዳት መጠናቸው ታይቶ በሽማግሌዎች የተወሰነ ብር ከፍሎ በዎማኖ ሤራ ተወስኖበት ወይም ፀድቆ ክፍያውን ይፈፅማል፡፡
አንቀፅ 12፡- የካ፡- አንድ የክስታኔ ቤተ ጉራጌ ተወላጅ የሆነ ሰው በአካባቢ ሽማግሌ፣በጥብ ወይም በጐርደና ስብሰባዎች በተለያዩ ጉዳዮች እንዲቀርብ ወይም የሚፈለግበትን እንዲፈፅም ሲጠየቅ ቀርቦ የተጠራበትን ጉዳይ ተረድቶ ለሚቀርብለት ጥያቄ መልስ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡
ሀ) ተፈላጊው ተወላጅ ወደ ተፈለገበት ጉባዔ እንዲቀርብ መጀመሪያ አንድ ሰው ይላክበታል፣
ለ) በመጀመሪያው ጥሪ ካልቀረበ ለሁለተኛ ጊዜ ሌላ ሰው ተጨምሮ እንዲቀርብ ይጠየቃል፣
ሐ) በሁለተኛውም ጥሪ ካልቀረበ ለሦስተኛ ጊዜ ሌላ ሰው ተጨምሮ እንዲቀርብ ይጠየቃል፣
መ) በሦስተኛውም ጥሪ ካልቀረበ ወይም የሚፈለግበትን ካልፈፀመና ከሸንጐ የተወከሉ ሊያቀርቡት ወይም ሊያስፈፅሙ ካልቻሉ እንደጉዳዩ ሁኔታና ደረጃ ቤቱ ይገባበታል፣
ሠ) ቤት የተገባበት ሰው በድርጊቱ ተፀፅቶ ሽማግሌዎችን በትህትና ካላቀረበ የሽማግሌዎችን መልዕክት ባለማክበሩ ቤቱ ውስጥ ከብት ታርዶ ይበላና ጉዳዩ ይታያል፣
ረ) በእንቢተኝነት ከቀጠለ ግን ሽማግሌዎቹ በሩን፣ደጁን፣አጥሩን ነቅለው የወግዙታል ወይንም ያስጠነቅቁታክ፤በመጨረሻም በፈፀመው ወንጀል ሽማግሌዎቹ ማስረጃ ሆነው በሕግ እንዲጠየቅና እንዲቀጣ ይደረጋል፣
ሰ) እንቢተኛ የሆነውና ከሕብረተሰቡ የተገለለው ተፀፅቶ ይቅርታ ከጠየቀ ባለመቅረቡ በተጠየቀበት ጉዳይ በየደረጃው ታይቶ ብርቱ ቅጣት ይፈፀምበታል፤በየደረጃው ያሉ የጐርደና ሽማግሌዎች ጉዳዩ ታይቶ የተሰጠው ቅጣት በሙሉ መፈፀሙ ሲረጋገጥ ውግዘቱና ማስጠንቀቂያው ሊነሳለትና ከማህበረሰቡ ሊቀላቀል ይችላል፣
አንቀፅ 13፡- ዎማኖ፡- ሌላ ሁለት መጠሪያ ስሞች አሉት፤(ራጋ) እና (ጌፈቼ ሤራ) ይባላል፡፡ ዎማኖ የሚለው ስም የአገር ሽማግሌዎች የወሰኑት ውሳኔ በትክክል ከጐርደና ሤራ ጋር የተጣጣመ መሆኑን የሚመለከቱ ባሕላዊ ዳኞች ይወክላል፤በተለይም የጉዳት ካሳ፣የወጪ መተኪያና ማካካሻን ለዕርቅ ሥርዓቱ መደረግ ያላባቸውን ባሕላዊ ሥርዓቶች በተመለከተ በትክክል መወሰናቸውን ይከታተላል ወይም ያረጋግጣል፡፡ በይበልጥ ደግሞ እውነቱ እንዲወጣና ዕርቁም በዚያው መሠረት መካሄዱን ለማረጋገጥ ጥረት ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም በአንድ ቤተሰብ ላይ ወይም በአንድ አካባቢ የተከሰተን መከራና ክፉ ነገር ያመጣው ምን እንደሆነ ሚስጥሩን ገልፀው ያወጣሉ፡፡
ሀ) የዎማኖ ሽማግሌዎች የአንድ ጉዳይ ማስረጃ ፍለጋ አይሄዱም፣የአገር ሽማግሌዎች ባቀረቡት ማስረጃ መነሻነት ውሳኔያቸውን ያስተላልፋሉ፣
ለ) ዎማኖ ከግለሰብ ጉዳዮች አልፎ አሳሳቢ የሆኑ የጋራ ችግሮችን እንደ የሰብል ውድመት፣ የተፈጥሮ አደጋ መቅሰፍት፣በአንድ አካባቢ የሰዎችም ሆነ የእንሰሳት በብዛት ማለቅ ወይም ሌሎች ለየት ያሉ ክስተቶችን ይመለከታል፤የአካባቢውን ቀደም ያለ ታሪክ ይመረምራል፤ይህን አስመልክቶም የአገር ሽማግሌዎች በጉዳዩ ምን እንዳሉ ይፈትሻል፤ይህ የኋላ ታሪክ የማወቁ ጉዳይ ምን አይነት ባሕላዊ ሥርዓት ይደረግ የሚለውን ለመለየትና በመጨረሻም (ኬርታ) እንዲካሄድ እስከመወሰን ድረስ ሊኬድ ይችላል፣
ሐ) የዎማኖ ሤራ የሚሰጠው (በገንዛደም) ጥብ (ጐሳ) ብቻ ሲሆን አመላመሉም ከገንዛደም ስድስት ሰዎች ይመረጣሉ፤ከተመረጡት ሰዎች በዕድሜ መብሰል በሂደት የፍርድ ሂደቱን ተግባር ይረከባሉ፣ሆኖም በአንድ ጊዜ የሚካሄድ ርክክብ የለም፤አንድ የዎማኖ አባል ይህን አገልግሎት የሚሰጠው የግብርና ሥራውን ጐን ለጐን እየሰራ ነው፣
መ) ዎማኖ በኬላ ከተማ በሚካኤል ቤተክርስቲያን ግቢ በየወሩ ይካሄዳል፤ማንኛውም ሰው ከየትኛውም ጐሳ፣ፆታ፣ሃይማኖት ይምጣ ችሎቱን ይከታተላል፤ውሳኔውንም ይቀበላል፤ ይፈፅማል፣
ሠ) ዎማኖ የሚጀመረው በምርቃት ሲሆን ይህም የሚቀርቡት ጉዳዮች ያለምንም አድልኦ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለማከናወን እንዲቻል ነው፡፡
አንቀፅ 14፡- ጋብቻ ወይም መተጫጨት፡- ጋብቻ የመልካም ኑሮ መሰረትና ቤተሰብን ማስቀጠል የሚችል ሆኖ ክቡር በመሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊደረግለት ይገባል፡፡
ሀ) ጋብቻ የሚፈፀመው በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት ላይ የተመሰረተና የቤተሰብም ፈቃደኝነት ያካተተ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ይሁንና ሁለቱ ተጋቢዎች ቢስማሙና እድሜያቸው ለጋብቻ ከደረሱ ወላጆች መከልከል የለባቸውም፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረግ ጋብቻ የተከለከለ ነው፤የተጋቢዎች ዕድሜም በሕግ መንግስቱ በተቀመጠው መሠረት ነው፣
ለ) ሁለቱ ተጋቢዎች ከመጋባታቸው በፊት የኤች.አይ.ቪ. (ኤድስ) በሽታ ቢያንስ 2 ጊዜ መመርመር ግዴታቸው ሲሆን ቤተሰብም ይህንኑ ማረጋገጥና የምርመራ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፤በምርመራ ወቅትም የሚመጡ ተመርማሪዎች ወደ ምርመራ ጣቢያ ሲመጡ ከሁለቱም ወገን ወንድምና እህት ከሌለም የቅርብ ዘመድ ከተመርማሪዎች ጋር አራት ብቻ ሆነው መገኘት አለባቸው፤ይህንንም ያልፈፀሙ ተጋቢዎች ካሉ ጋብቻ መፈፀም አይችሉም፤ያለመመርመራቸው ከታወቀ ማንም ግለሰብ ወደ ሰርግ ቤት መሄድ የተከለከለ ሆኖ ይህንን ተላልፎ የፈፀመ በባሕላችን መሠረት ደጋሽ ብር 1,500.00 (አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር) ታዳሚው እያንዳንዱ ብር 100.00 (አንድ መቶ ብር) ይቀጣል፣
ሐ) በበሽታው የተጐዱ ወገኖችን ድጋፍና እንክብካብ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ህብረተሰብ ሲሆን የማስተማርና ሳቡኘት (ዕድር) ከሞት በኋላ መቅበር ብቻ ሳይሆን በሕይወት ሳሉ የመርዳት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፣
መ) በከተማ አካባቢ በሥራ ተሰማርተው ያሉ ጥንዶች ወይም ባልና ሚስቶች ከቆይታ በኋላ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) መከላከያ የመጠቀምና የመመርመር ገዴታ አለባቸው፤ይህ ሳይፈፀም ቢቀር በባሕላችን መሠረት ብር 800 (ስምንት መቶ ብር) ይቀጣል፣
ሠ) የቤተ ዘመዶችን መጋባት በባሕልም ይሁን በሕግ የተከለከለ ነው፤በቤተሰብ ሲቆጠር እስከ 7 ቤት ትውልድ ድረስ መጋባት አይቻልም፤ይህንንም ተላልፎ የተገኘ 600 ብር ይቀጣል፣
ረ) የቸግ (ሚጁ) የሚሉ ሌሎችም ከጋብቻ በፊት የሚፈፀሙ ስርዓቶች እንዳሉ ሆነው ወደ ልጅቷ ቤት የሚሄድ ሽማግሌዎች ከሁለት የልበለጡ ሆነው ምንም ድግስ ሳያስፈልግ በአነስተኛ ወጪ በባሕል መስተንግዶ ከ200 ብር ያልበለጠ መከናወን አለበት፤ከዚህ ውጪ የተከለከለ ስርዓት ነው፣
አንቀፅ 15፡- የሚት ደኦት (ጥሎሽ) ፡- ጥሎሽ ለብዙ ጋብቻዎች አለመሳካትና በአቅም ማነስ ምክንያት ጥሎሽ ላለመክፈልና በጋብቻ ሳቢያ ለሚወጣ ወጪ ፍራቻ የጠለፋ መስፋፋትና መንስዔ እየሆነ ነው፡፡ በሌላ በኩል ክቡር ጋብቻውን በገንዘብ አማካኝነት እንደሚፈፀም ተደርጐ በመወሰድ የሁለቱ ተጋቢዎች ቤተሰብ ይህንኑ በመገንዘብ ለጥሎሽ ብር 1000 (አንድ ሺህ ብር) ብቻ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
1. ለሙሽሪት የሚሰጥ ስጦታና አልባሳት በተመለከተ፡-
ጋብቻ የሚመሰረተው ተጋቢዎቹ በቀጣዩም ኑሮዋቸው ላይ ችግር እንዳይፈጠር መታሰብ ስላለበት በሙሽራው መሰጠት ያለበት ከዚህ ውጪ ከላይ የተገለፁት ችግሮች ስለሚያስከትል የተከለከለ ነው፡፡ ይሁንና ከሙሽሪት ወይም ከሙሽራው ከላይ የተጠቀሰውን ባይፈልጉ አይገደዱም
2. ለሰርጉ የሚደረግ ድግስ በተመለከተ፡-
ሀ) ድግሱ የሁለቱ ተጋቢዎች ቤተሰብ አቅም ያገናዘበ መሆን አለበት በወረዳችን ሰርግ መደገስ ባሕላችን ቢሆንም አሁን በሚታየው መልኩ ቤተሰብና ተጋቢዎችን ከመጠን ባለፈ አቅም አሳጥቶ በሚያፈናቅል ሁኔታ በግልፅ እየታየና የተመሰረተውም ትዳር እያፈረሰና በችግሩ ምክንያት ለወንጀል መከሰት መንስዔም ጭምር እየሆነ ከራሱ አቅም ጋር የተመጠነ ያለ ምንም ይሉንታ እና ተፅዕኖ ቤቱ ባፈራው አንሰተኛ መስተንግዶና ወጪ መፈፀም አለበት፤ከአቅም በላይ ድግስ ደግሶ ሕዝብ እየጠሩ ማብላት ክልክል ነው፡፡
ለ) በሰርግ ጊዜ ልጅቷ ቤት ሲኬድ ለሳንቃ መዝጊያ መክፈቻ ተብሎ የሚጠየቅ ብር ወይም ሻሽ ሲጣል የሚጠየቅ ብር ጐጂ ስለሆነ መቅረት አለበት፤ይህን ፈፅሞ የተገኘ በባሕላችን 700 ብር ይቀጣል፡፡
ሐ) ጫጉላም ከሰርጉ ቀን በፊትም ሆነ ኋላ በአግባቡ መሆን አለበት፣

3. የሙሽራው የመንቀሳቀሻ ሠዓት በተመለከተ፡-
በሰርግ ዕለት ያለ ሠዓት በመነሳትና በመንገድ በሙሽራዎችና በአጃቢዎች ላይ እንግልት ከማስከተሉም በላይ የኤች.አይ.ቪ ተጋላጭነትን እያባባሰና ለሌሎች ችግሮች የሚጋብዝ ስለሆነ የጭለማ ጉዞ ባሕልም የሌለን በመሆኑ ሙሽራው ወደ ሙሽሪት ቤት መነሳት ያለበት ከቀኑ 6፡00 ሠዓት ሆኑ ከቀኑ 10፡00 ሠዓት ከሙሽራዋ ቤት መነሳት አለበት፡፡ በጣም የራቀ ከሆነ ሠዓት በማስተካከል ቀደም ብሎ መነሳት አለበት፤ከዚህ ውጪ የተጓዘ በባሕልም ሆነ በሕግ ይቀጣል፡፡
4. አጃቢዎችን በተመለከተ፡-
የአጃቢዎች መብዛት ለሁለቱም ተጋቢዎች ጠቀሜታ የሌለው በመሆኑና የኢኮኖሚ ጫና ስለሚያመጣ ከ15 ሰው ያልበለጡ መሆን አለባቸው፤ከዚህ በላይ ያስከተለም ሆነ የተቀበለ በባሕላችን ወይም በሕግ ይቀጣል፡፡
5. የሙሽሪት የኮሶ ስርዓት፡-
ሀ) የኮሶ ስርዓት ጠቀሜታ የሌለው ስለሆነና አላማውም በጫጉላ ጉዞ ሙሽሪት እንድትደክምና የወንዱን የበላይነት እንዲረጋገጥ ተብሎ የሚደረግ ሲሆን ከጥቅሙም ጉዳቱ ስለሚያመዝን መቅረት አለበት፤ከኮሶ ጋር ተያይዞ የሚደርስ ድግስና ስርቆቸ መቅረት አለበት፤ይህንን ፈፅሞ የተገኘ በባሕላችን (በሕግ) ይቀጣል፡፡
6. ኡርጋ በተመለከተ፡-
በኡርጋ ጊዜ 2ቱ ሙዜዎች ብቻ መሄድ አለባቸው፡፡ ለዚህ ተብሎ ድግስ መደገስ የተከለከለ ነው፤ከሁለቱ ሚዜዎች ውጪ የሙሽሪት ቤተሰቦችም መቀበል የለባቸውም፤ ከዚህ ውጪ የፈፀመ በባሕል (በሕግ) ይቀጣል፡፡
7. አውታ (አፍታ) በተመለከተ፡-
አውታ ወጣቶች ወደ አልተፈለገ ድርጊት እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ በተለይ ሴት ልጆች እየተደፈሩ በመሆኑና ለኤች. አይ. ቪ (ኤድስ) የሚያጋልጥ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ስለሆነም ወንድምና እህት ብቻ ቁጥራቸውም ከ3 ያልበለጠ መሄድ አለባቸው፡፡ ወንድምና እህት ከሌለ 2 ወንዶች ብቻ እንዲጠይቁ መደረግ አለበት በጥየቃ ጊዜ ምንም የተለየ ድግስ መደገስ የተከለከለ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚፈፀም የሙሽራ ቤተሰብም ሆነ ላኪው ቤተሰብ በባሕላችን መሠረት ይቀጣል፡፡

8. ቅቤ መቀባት በተመለከተ፡-
ሀ) ቅቤ መቀባት ለሁለቱም ወገኖች የሚሰጠው ጠቀሜታ ስለሌለና ጉዳቱ ከፍተኛ እየሆነ ስለመጣ ከ5 ሴቶች በላይ መሄድ እንደሌለባቸውና በዕለቱ መመለስ አለባቸው፡፡ ይህን የተላለፈ ብር 2000 (ሁለት ሺህ ብር) ይቀጣል፣
ለ) የአገቡ ሙሽራዎች ወደ አባታቸው ቤት ተመልሰው 3 ወር ይቀመጣሉ፡፡ ይህ አጉል ባሕልና ጐጂ እየሆነ የመጣ ስለሆነ ከባልዋ ጋር ብቻ ለመልስ መጥታ አብራ መመለስ አለባት፤ከዚህ ውጪ ፈፅሞ የተገኘ 300 ብር (ሦስት መቶ ብር) ይቀጣል፣
9. መልስ (አንገትኧግዳን)፡-
መልስ (አንገትኧግዳን) ወቅት የልጅቷ ቤተሰብም ሆነ የልጅ ቤተሰብ ለተጨማሪ ወጪና ጉዳት የሚጋብዝ ነው፡፡ ስለሆነም ሁለቱ ተጋቢዎች ከ2 ሚዜዎቻቸው ጋር 100 ብር (አንድ መቶ ብር) ብቻ በመያዝ በአንድ ቀን ደርሰው መመለስ አለባቸው፡፡ የልጅቷ ቤተሰቦችም በጣም ባነሰ ወጪና ዝግጅት ቤት ያፈራውን ብቻ አዘጋጅተው ሊሸኙ ይገባል፡፡ ምን አልባት እርድ እንኳን ቢያስፈልግ በግ ብቻ አርደው ማስተናገድ አለባቸው ከዚህ ውጪ ይዞ የሄደም ይሁን የተቀበለ በባሕላችን መሠረት የተከለከለና የሚያስቀጣ ነው፡፡ ቅልፈትና ተከቦቸም ከነጭራሹ ጠቀሜታ የሌለው ስለሆነ እንዲቀር ተወስኗል፡፡
10. ከሰርግ ደስታ ጋር በተያያዘ የመሳሪያ ተኩስ በተመለከተ፡-
ከሰርግ ደስታ ጋር በተያያዘ ደስታ ሆነ በሌላ ደስታና እንዲሁም በሐዘን፣በለቅሶ መሳሪያ መተኮስ የተከለከለ ነው፡፡ ይህንን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በባሕላችን ተቀጥቶ መሳሪያው ተወርሶበት ለመንግስት ገቢ ይደረጋል፡፡ ግለሰቡ ከወረዳው ወጪ ቢሆን በህግ ተከሶ ይጠየቃል፡፡ አንቀፅ ሦስትን ጠቅላላ የተላለፈ ብር 1800 (አንድ ሺህ ስምንት መቶ ብር) ይቀጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ ድርጊቱ ከብደት እየታየ ከ15-24 ሽማግሌዎ የካ ተልኮበት ያስተናግዳል፡፡
አንቀፅ 16፡- አዳብና በተመለከተ፡- የአዳብና ስርዓት በአሁኑ ወቅት ድሮ ከነበረው ባሕል በተለየ መልኩ እስከ ማምሻ ድረስ በመቆየቱ ለጠለፋ ለመደፈር ትልቅ በር ከፋች እየሆነ ከመሆኑም በላይ ለኤች. አይ. ቪ. (ኤድስና) ተዛማጅ በሽታዎች መስፋፋትም ትልቅ መንስዔ እየሆነ መጥቷል፤ስለሆነም አዳብና ከነጭራሹ ይጥፋ ባይባልም አዳብናን ጨምሮ ከባሕል ጋር የተያያዙ ጭፈራዎችና ጨዋታዎች እስከ ቀኑ 9፡00 ሰዓት ድረስ ጥበቃ እየተደረገላቸው ማብቃትና መብትን አለበት፡፡ ይህንንም በየአካባቢው ባሉ የባሕል ሽማግሌዎች የመንግሥት አካላት ጭምር በጋራ ጥበቃ እያደረጉለት በሰዓቱ የሚበተኑበት ሁኔታ እየፈጠረ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ያሰማራ አባትና እናትም ሆነ ግለሰብ በባሕላችን መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ አንቀፅ አራትን ተላልፎ የተገኘም እስከ ብር 300 (ሦስት መቶ ብር) ይቀጣል፡፡
አንቀፅ 17፡- ከበድ ያሉ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፡-
ሀ) ጠለፋና ሸኮካንቾ በጤና በአካልና በስነልቦና ላይ የከፋ ጉዳት የሚያስከትልና ትልቅ ወንጀል ስለሆነ የጠለፈ የተባበረና የደበቀ በባሕላችንና በሕግ ይቀጣል፣
ለ) ይህንን ወንጀል የፈፀመ፣የተባበረ በሕግ ቀርቦ እንዲጠየቅ የባሕል ሸንጐ አስፈላጊውን ጥረት ያደርጋል፤በሕግ ለመጠየቅ ያልተሟሉ ነገሮች ካሉ በባሕላችን መሠረት ጠለፋ ፈፃሚውና ተባባሪው ነፃ የሚያወጣቸው 5 (አምስት) ሰዎች እንዲምሉላቸው ተፈቅዶ ነፃ ካለወጧቸው ወይም ካልማሉላቸው ዋና ጠላፊው በባህል ሽማግሌዎች ብር 10,000.00 (አስር ሺህ ብር) ቅጣት ተቀጥቶ ለልጅቷና ለቤተሰቦቿም የሞራል ካሳ ብር 2,500.00 (ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር) ቅጣት ይከፍላል፣
ሐ) በዚህ ጉዳይ የተባበሩ፣የደበቁ፣መጠለያ የሰጡና ያስታረቁ ግለሰቦች እያንዳንዳቸው ብር 800.00 (ስምንት መቶ ብር) ይቀጣል፣
መ) የውርስ ጋብቻ፣የሴት ልጅ ግርዛት፣እንጥል መቁረጥ፣ጥፍር መቅፈፍ፣ግግ መንቀል፣ጐሮሮ ማስቧጠጥ፣ንቅሳት፣የአይን ቆብ መብጣት፣አላስፈላጊና ለኤች.አይ.ቪ. (ኤድስ) በሽታ መተላለፊያና መንስዔ ስለሆኑ ይህንን ተላልፎ የተገኘ በሕግ የመጠየቁ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ ብር 1,200.00 (አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር) ይቀጣል፣
አንቀፅ 18፡- ቢተን ዎውጣ (ጐጆ መውጣት)፡- ከወላጆቻቸው ይኖሩ የነበሩ ወንድና ሴት በክስታኔ ቤተ ጉራጌ የጋብቻ ደንብና ስርዓት በሚከተሉት እምነት መሠረት ተጋብተው ጐጆ ሲወጡ ወላጆች ወይም ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ቢተን (ጐጆ መውጫ) መሥጠት የተለመደ ሲሆን ይህም መቀጠል አለበት፡፡ በተለይም የወንዱ ወላጆች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ልጆቻቸው ቢተን (ጐጆ) እንዲወጡና እንዲቋቋሙ የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡
አንቀጽ 19 ብሸ (ለቅሶ፣ሀዘን)
፡- በክስታኔ ቤተ ጉራጌ ዕድሜን፣ፆታን፣ማዕረግን፣ታሪክን ወዘተ. መሠረት ያደረገ የለቅሶ ስርዓት እንዳለው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ይህ ስነስርዓት እየተጠበቀ ባለመሆኑ፡-
ሀ) የቁም ብሽ፡- እንደሟቹ የማህበራዊ አገልግሎትና ታዋቂነት ሁኔታ የሚፈፀም ስለሆነ ይህንኑ ሽማግሌዎችን ለመጠየቅ የነበረው ስርዓት ተጠብቆ መቆየት አለበት፣
ለ) በለቅሶ ወቅት ለሃዘን መስተንግዶ ተብሎ የሚወጣው ወጪ መጠነኛና አቅምን ያገናዘበ መሆን አለበት፣
ሐ) ለጉራና ሃብት የሌላቸውን ሰዎች ዝቅ አድርጐ ለማሳየት የሚደረግ አላስፈላጊ ወጪ መቀጠል የለበትም፤መስተንግዶውም ለሁሉም እኩል መሆን አለበት፣
መ) የለቅሶና ተዝካር ተፈፃሚነት፡- በጐርደና ሤራ የተካተቱት የለቅሶና የተዝካር ደንቦች በክስታኔ ጉራጌ ተወላጆች ሁሉ መከበር አለባቸው፣
ሠ) እሳሪየ፡- ከቀብር በኋላ የሟች ቤተሰብ ወይም ልጆች ሟቹን መንከባከባቸውን ወይም አለመንከባከባቸው የቀበረው ለቀስተኛ ተሰብሰቦ በእሳሪየ ዳኞች አማካኝነት የሟች ጐረቤት የሆኑትን ሟቹን መንከባከባቸው ወይም አለመንከባከባቸው በመጠየቅ ጐረቤቶቹ መንከባከባቸውን ከመሰከሩላቸው እንዲመረቁና ቅቤ እንዲቀቡ በማድረግ ይመረቃሉ፤ በተጨማሪም አለመንከባከባቸው ከተመሰከረባቸው ቤተሰቦቹ ወይም ልጆቹ ከለቅሶ ፊታቸውን እንዲያዞሩና ወደ ቤታቸው ብቻቸውን እንዲመለሱ በማድረግ፣በመውቀስ፣በማውገዝ ዳኞቹና ሕዝቡ ያሰናብታቸዋል፤ወደ ሟቹ ቤትም አይመለሱም እንዲያፍሩም ይደረጋሉ፡፡ ይህ ባሕል ወላጆች እንዲጦሩ እና ልጆችም ወላጆቻቸውን እንዲንከባከቡ የሚያደርግ በመሆኑ መቀጠል አለበት፣
ረ) የእሳሪየ ዳኞች፡- በየአገሩ በጐሳቸው የተመረጡ በመሆናቸው ይህን ሕዝቡ የጣለባቸውን ኃላፊነት በማጠናከር እንዲቀጥሉበትና ሕዝቡም ከበሬታ ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑን አውቀው በለቅሶ ወቅት ራሳቸው ይህንን ጥሩ ባሕል እንዲቀጥል ማድረግ አለባቸው፣
አንቀፅ 20፡- አካባቢን መንከባከብ፡-
ሀ) ባሕርዛፍ ብዙ ውሃ ስለሚያስፈልገውና ሥሩም ረጅም ቦታ ሄዶ ውሃ ስለሚስብ ከእንሰትና ከሌሎችም ሰብሎች ራቅ ብሎ መተከል አለበት፣
ለ) በምንጭ ውሃ አጠገብና በሁለት ባለይዞታዎች ወሰን ላይ ባሕርዛፍ መተከል የለበትም፣
ሐ) የእንሰት፣የጐመንና ሌሎችም የምግብ ሰብሎችን ቦታ በማያሻማና ዕድገታቸውን በማይጐዳ ወይም ደረጃቸውን ዝቅ በማያደርግ ሁኔታ ብቻ መተከል አለባቸው፣
መ) እንሰት በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥና በውጭ አገር በከፍተኛ ደረጃ ታዋቃና ተፈላጊ እየሆኑ የመጡት አጥሚጥ (የቆጮና የቡላ) ምርቶች ከምንጫቸው ተዳክሞ ስለሚታይና አሳሳቢም ስለሆነ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፣
ሠ) እንሰት የተፈጥሮ ችግሮችን መቋቋም የሚችል በመሆኑና ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ በብዛትና በጥራት እንዲመረት የሚመለከታቸው በሙሉ ያልተቆጠበ ጥረት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለባቸው፡፡ አርሶ አደሩም እውነታውን ተረድቶ ምርቱን ሊያጐለብት ይገባል፣
ረ) ምሁራንም የእንሰት ዕድገትን የሚያፋጥኑ፣እንዲሁም የሚያጠቁትን በሽታዎች ለመከላከልና ብሎም ለማጥፋት የሚያስችል ጥናቶችን በማድረግና የጥናት ውጤቶችንም ወደ ታች በማውረድ ሁሉም ተባብሮ የእንሰት ምርት ዕድገት እንዲጐለብት ማድረግ ይጠበቅበታል፣
አንቀፅ 21፡- ማሕበራዊ መተጋገዞች፡-
1. ዕድርና እቁብ፡-
ዕድርና እቁብ በተለይ በጉራጌ ክልል ለልማት ሥራዎች በድጋፍ ሰጪነቱ ከፍተኛ ሚና የተጫወተና በመጫወትም ላይ የሚገኝ ሲሆን የጉራጌ ልዩ መታወቂያ ስለሆነ ሁለቱም ከዚህ በበለጠ የልማት ማንቀሳቀሻ እና መረዳጃ ሞተሮች መሆን እንዲችሉ ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማደራጀት መቀጠል አለበት፣
2. ዎቻ፡-
ሀ) ዎቻ ከብት የተሰጠው ሰው ላሚቷን በመንከባከብ ስትወልድ ወተቷን በመጠቀም የማርባት ዘዴ ነው፣
ለ) ዎቻ ሰጪው ተቸግሮ ወይም በሌላ ምክንያት ዎቻ የተሰጠው ሰው በአንድ ዙር ወተቷን ሳይጠቀም የሚወስድበት ከሆነ ለተወሰደበት ሰው ብር 1,000.00 (አንድ ሺህ ብር) ካሳ ከፍሎ ላሚቷን መውሰድ ይችላል፣
ሐ) ዎቻ የተሰጠው ሰው በአንድ ዙር ወተቷ ከተጠቀመ በኋላ ባለዎቻው ላሚቷን ለመውሰድ ጠይቆ አልሰጥም ካለ ዎቻ ሰጪውን በማጉላላቱ ብር 300.00 (ሦስት መቶ ብር) ተቀጥቶ ላሚቷን እንዲመልስ፣
መ) ለግርፍ የተሰጠ ወይፈን ግርፍ ሰጪው ወይፈኑን ለመመለስ ብር 1,000.00 (አንድ ሺህ ብር) ከፍሎ መመለስ ይችላል፣
3. ቆት፡-
ቆት ከዎቻ ስርዓት የተለየ ስለሆነ በሁለቱ ተዋዋዮች መካከል በሚደረግ ስምምነት መሠረት መፈፀም አለበት፡፡
4. ጥጃ፡-
ከአምስት ወንዶች በላይ በመደራጀት በየተራ ድግስ እየተደገሰ የእንሰትም ሆነ ሌሎችም ሥራዎች በጋራ ተባብሮ በአንድ ቀን ሥራን የማጠናቀቂያ ዘዴ ነው፡፡
5. ግቦ፡-
ከአምስት ወንዶች (ሴቶች) በታች በመደራጀት በየተራ በመግባባት አብሮ የሚሰሩበት የሥራ ሥልት ነው፡፡
6. ጂጊ፡-
አንድ አቅመ ደካማ የሆነ ወይም ባለሃብት የአካባቢውን ሕብረተሰብ የጉልበት ሥራ እንዲረዳ በመለመን የእንሰት ሥራም ይሁን ሌሎችም ሥራዎች ድግስ በመደገስ እንዲሰራለት የሚያደርግበት ዘዴ ነው፡፡

7. ውሳቻ፡-
ከአምስት ሴቶች በላይ በመደራጀት በየተራ ድግስ እየተደገሰ የእንሰትም ሆነ ሌሎችም ሥራዎች በጋራ ተባብሮ በአንድ ቀን ሥራን የማጠናቀቂያ ዘዴ ነው፡፡

8. ውጆ፡-
እስከ አምስት ሴቶች በመደራጀት የወተትና የቅቤ እቁብ (ማህበር) የመረዳጃ ዘዴ ነው፡፡
አንቀፅ 22፡- አልኮልና ሌሎች ጐጂ እፆች፡-
1. የአልኮል መጠጥ፡- አልኮል በተለይ አረቄ በጉራጌ ሕብረተሰብ ላይ የሥራ ባሕሉን በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰና በጤናውም ላይ ጉዳት እያስከተለ በመምጣቱ ጐጂ መሆኑን በጐርደና ሤራ ለሁሉም ተወላጅ ጐጂነቱን በማስረዳት ከመጠጣት እንዲቆጠብ ግንዛቤ መፍጠር፡፡
ሀ) እርሻ በሚታረስበት ጊዜና ቦታ፣
ለ) ሽምግልናና ዳኝነት በሚታይበት ጊዜና ቦታ፣
ሐ) ቤት ጊዜና ቦታ፣
መ) በቀብርና ለቅሶ በተቀመጡበት ቦታ፣
ሠ) የጋብቻ ስርዓት በሚፈፀምበት ቦታ፣
ረ) በወንዶችና በሴቶች የደቦ ሥራ ቦታ…. ወዘተ.
ከላይ በተዘረዘሩትና በሌሎችም ማሕበራዊ ግንኙነቶች ቦታ አረቄ ከመጠን በላይ ማቅረብና መጠጣት እጅግ በጣም ጐጂ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፤እንዲሁም ይህን በሚፈፅሙ ላይ የአካባቢ ሽማግሌዎች ማውገዝ አለባቸው፡፡
2. ጫት መብላት (መቃም)፡- በአሁን ደረጃ በከተሞች አካባቢ በወጣቱና በአንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ እየተለመደ የመጣ በመሆኑ እንደአረቄ ሁሉ በጉራጌ ብሄረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ ሊታሰብበትና ሊታረም እንደሚገባ በምክር ቤቶች ሁሉ ምክር እንዲሰጥበት ሆኖ ከላይ በተራ ቁጥር 1 ከሀ-ረ በተጠቀሱት ቦታዎችና በት/ቤቶች እንዲሁም በሌሎች ተቋማት ውስጥ መጠቀም የተከለከለ ሲሆን ይህን በሚፈፅሙ ላይ ክትትል በማድረግ የአካባቢ ሽማግሌዎች ሊያወግዙት ይገባል፡፡
3. ሲጃራና ሌሎች ጐጂ እፆች፡-
ሀ) ሲጃራ ማጨስ ለጤና ጠንቅ መሆኑ ታውቆ ህብረተሰቡ ሲጋራ ባለማጨስ ጤንነቱን እንዲጠብቅ ብርቱ ማሳሰቢያ መስጠት፣
ለ) በስብሰባ ቦታ፣በት/ቤቶች አካባቢ፣በመንግሥት መ/ቤቶች አካባቢ ሲጃራ ማጨስ በፍፁም የተከለከለ መሆኑን፣
ሐ) እንደ ሃሺሽ፣ሺሻና የመሳሰሉት ጐጂ እፆች በማናቸውም ጊዜና ቦታ መጠቀም የተከለከለ በመሆኑ ህብረተሰቡ እየተከታተለ ማህበራዊ እርምጃ እንዲወስድ ተወስኗል፣
አንቀፅ 23፡- የቤት አሰራር፣የጐርደና ሞጨ፣የድንበር እማየ፡-
1. የክስታኔ ቤተ ጉራጌ ቤት አሰራር፡-
የክስታኔ ቤት አሰራር ከጥንት ጀምሮ ከውጪም ሆነ ከውስጥ የሚገነባው ግንባታ የቤተሰብን ድርሻ ያገናዘበ ወይንም የሚወክል በመሆኑ ይህንኑ እንዲቀጥል ሆኖ የነፋስና የብርሃን መስኮት እንዲኖረውና ሌሎችም ጠቃሚ ማሻሻያዎች ተደርገውበት ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ ማሳወቅ፤ማስገንዘብ፡፡

2. የጐርደና ሞጨ፡-
ሀ) በክስታኔ ቤተ ጉራጌ የጐርደና ሞጨ (መንገድ) አከላለልና አጠባበቅ ሤራ (ደንብ) አለው፤በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙ ቦታ ደንቡ እየተጣሰ በመንገዱ ላይ አጥር በማጠር፣ቤት በመሥራት፣አትክልትና ዛፍ በመትከል አየጠፋ ስለሆነ ይህ አድራጐት ተገቢ ስላልሆነ የአካባቢው ሽማግሌዎች ጥንት የነበረውን የጐርደና ሞጨ በመለየትና በማስጠበቅ ማቆየት አስፈላጊ ነው፣
ለ) የጐርደና ሞጨ (መንገድ) አገልግሎት የጋራ እንደመሆኑ መጠን የሚወሰነው በተጠቃሚው ጠቅላላ ሕዝብ እንጂ በአንድ ተገልጋይ ብቻ ስላልሆነ አገሩ ወይም ቀበሌው በሽማግሌዎች በመታገዝ ጥንት የነበረውን የጐርደና ሞጨ (መንገድ) እንዲከበር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፣
ሐ) የመንደር ወይም የቤተክርስቲያን መንገዶች የሕዝብ መተላለፊያ በመሆናቸው በአንዳንድ አካባቢ እየተዘጉ ስለሆነ በነበረው ባሕል መሠረት መንገዶቹ ሳይዘጉ ሕዝብ እንዲገለገልባቸው እንዲደረግ የአካባቢው ሕብረተሰብ መተባበር አለበት፣
3. የድንበር እማየ (ድንጋይ)፡-
የሁለት ይዞታዎችን መሬት፣የጐርደና ሞጨ እንዲሁም ከሌሎች ይዞታዎች የሚለየው በድንበር ድንጋይ በመሆኑ ይህንን ድንበር ማክበርና ማስከበር ግዴታ ሲሆን ድንበሩን በቀንም ሆነ በሌሊት የነቀለ ሰው ብር 300.00 (ሦስት መቶ ብር) ቅጣት ከፍሎ የድንበሩን ድንጋይ ወደነበረበት የመመለስ ግዴታ አለበት፤አፈፃፀሙም አለመተማመን ከፈጠረ በ5 (አምስት) ሽማግሌዎች አማካኝነት ለፌ በመጥራት ወይም መሃላ በመፈፀም ይተገበራል፡፡
አንቀፅ 24፡- የባሕል ቅርሶችን የመጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት፡-
ሀ) የጉራጌ ባሕል ቅርስ የሆኑ ዕቃዎች በመጥፋት ላይ በመሆናቸው ዕቃዎቹን ሁሉ የሚያካትት ሙዚየም መሥራት ጊዜ፣ሃብትና ድርጅት የሚጠይቅ በመሆኑ ሕዝቡ ብርቱ ጥረት በማድረግ ቅርሶቹን የመጠበቅና የመንከባከብ እንዲሁም የማስጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት አለበት፣
ለ) ህብረተሰቡ በየአካባቢው ያሉ ታሪካዊ ቦታዎችን፣የተፈጥሮ መስህቦችን፣ትክል ድንጋዮችን፣ የሃይማኖት ቦታዎችን፣የመናፈሻ ቦታዎችና የጐርደና ሸንጐ መሰብሰቢያ ቦታዎች የመጠበቅና የማደራጀት ግዴታና ኃላፊነት አለበት፣
ሐ) ያሉት ዋና ዋና የቅርስ ዕቃዎች በእንክብካብ እንዲጠበቁ ሆኖ የጠፉትንም በአይነታቸው አስመስሎ በመስራት ቢሸጡ ገቢ ስለሚያስገኙ እንዲሰሩ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፣
አንቀፅ 25፡- ባሕላዊ ህክምና፣ስፖርትና ኪነት
1. ባሕላዊ ህክምና፡-
ሀ) ህብረተሰቡ በባሕላዊ ህክምናዎች ከመጠቀሙ በፊት በተቻለ መጠን በዘመናዊ ህክምና እንዲጠቀም ማበረታታት ይገባል፣
ለ) የባሕል ህክምና ሰጪዎች፣መርፌ ወጊዎች በሚያክሙበት ጊዜ መጠጥ እንዳይወስዱ ጥንቃቄ ከማድረግ ባሻገር የአጥንት ስብራት፣የወለምታና ሌሎችም ህክምና የሚሰጡ እውቅ የልምድ ባለሙያዎች፣አዋላጆች አሰራራቸውና መድሃኒት አሰጣጣቸው በህብረተሰቡ ጤና ላይ አደጋ እንዳያስከትል የጤና ትምህርት እንዲቀስሙና አገልግሎታቸውን በጥንቃቄ እንዲሰጡ እንዲደረግ፣

2. ስፖርት፡-
ስፖርት በጉራጌ ባሕል ውስጥ ሊበረታቱና ሊጠበቁ የሚገባቸው ስፖርቶች ብዙ ቢሆኑም ያለባቸውን ድክመት (ጉዳት) እንዳያስከትሉ ታርመው በተሻሻለ ሁኔታ መቀጠል አለባቸው፤እነርሱም አንቃት (ሩር)፣የአጋት ዝላለ፣ሰዲቃ፣ሰባ፣የፈረስ ጮታ፣መጆ አራጆ፣ ዎቅለ፣ቀጨሌ፣የምድር ዝላለና ግጂላ ሌሎችም እየተጠኑ ግልጋሎት ላይ የሚውሉበት ሁኔታ እንዲመቻች፡፡

3. ኪነጥበብና ኪነት፡-
ሀ) በክስታኔ ቤተ ጉራጌ ባሕል ደርስ (ዘፈን)፣ውንቂትና ዎግ ሌሎችም ማህበራዊ ከበሬታዎች እንዲዳብሩ በአንፃሩም ማህበራዊ ነውሮች እንዲከስሙ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ፣ልጆችም ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩን እንዲጦሩ የልማት ሥራዎቸ እንዲጠናከሩ በጥናት በተደገፈ ሁኔታ እንዲዳብር መደረግ አለበት፣
ለ) ልዩ ልዩ ባሕላዊ ጨዋታዎችና ኪነጥበባት ተሰብስበውና ተጠንተው ሕይወት ሊዘሩ በሚችሉበት ሁኔታ መቀረፅ አለባቸው፣
አንቀፅ 26፡- የጐርደና ሸንጐ መሰብሰቢያ ጊዜ፡-
ሀ) አጠቃላይ የጐርደና ሸንጐ ምክር ቤት በምክር ቤቱ ደረጃ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ሳያጋጥሙ ሽማግሌዎች ተጠርተው በዓመት 3 (ሦስት) ጊዜ እንዲሆንና አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥም በጥሪ መሠረት መሰብሰብ ይቻላል፣
ለ) በስብሰባ ወቅት ሰዓት ማክበር ተገቢ በመሆኑ የዓለማችን ስልጣኔ ከደረሰበት ደረጃ አኳያ ጊዜ ፍፁም ወርቅ ስለሆነ ሁሉም የሸንጐ አባላት ሰዓት አክብረው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፣
ሐ) ሸንጐ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት መረጃዎችን በአግባቡ ማቅረብና ማብላላት፣ የሃሳብ ሙሉ በሙሉ ማንሸራሸር ተገቢ ሲሆን የማያስፈልጉ ድግግሞሾችን በማስቀረትና ጊዜ በመቆጠብ ከመሰላቸት የፀዳ አቋም ያለው ውሳኔ ማስገኘቱ የጋራ ኃላፊነት በመሆኑ ሁሉም የሸንጐ አባል ሁኔታዎችን ሊያከብር ይገባል፣
መ) የስብሰባው ውጤት በሰነድነት በመመዝገብ በተለይም የሚተላለፉ ውሳኔዎች ወደታችኛው አካል ለማውረድና ለታሪክ መዘክርነት፣ለአርአያነት፣ሸንጐውን ለማዳበርና ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚኖራቸው በቋሚ መዝገብ እየተመዘገቡና በትክክል ለመስፈራቸው ቢያንስ በሽማግሌዎች፣በሰብሳቢና በፀሐፊ ፊርማ እየተረጋገጠ በሰነድነት መያዝ አለባቸው፣
አንቀፅ 27፡- ከቅጣት የሚገኝ ገቢ አጠቃቀም፡-
ሀ) በጐርደና ሸንጐ በየደረጃው የሸንጐውን ሤራ (ደንብ) ከጣሱ ተወላጆች የሚሰበሰበው የቅጣት ገንዘብና ሸንጐው በእርዳታና በተለያዩ ሁኔታዎች የሚያገኘውን ገቢ (ገንዘብ) ለአካባቢው ልማት ሥራ መዋል አለበት፣
ለ) የገቢና ወጪ ሁኔታዎች በዝርዝር በሕጋዊ ደረሰኝ ከተመዘገቡ በኋላ ሸንጐው ለሚወስናቸው ውሳኔዎች ማስፈፀሚያ ጭምር ማዋል ይገባል፣
አንቀፅ 28፡- የጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) ስለማሻሻል፡-
ይህ የተሻሻለው የጐርደና ሸንጐ በሙሉም ሆነ በከፊል የሚሻሻሉ ወይም ሌሎች የሚጨመሩ ጉዳዮች ሲኖሩት ከየአገሩ ሕዝብ በእኩል ቁጥር በሚወከል የጐርደና ሸንጐ ጠቅላላ ምክር ቤት ሊሻሻል ይችላል፡፡
አንቀፅ 29፡- የጐርደና ሸንጐ ሤራ (ደንብ) የሚፀናበት ጊዜ፡-
ይህ የጐርደና ሸንጐ መተዳደሪያ ሤራ (ደንብ) ከ ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡