ምድረ ከብድ አቡነ ገበረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም

አቦ

ኢትዮጵያ ካሏት ጥንታዊና ታሪካዊ ቤተክርስቲያናትና ገዳማት መካከል የምድረ-ከብድ አቦ ገዳም አንዱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ገዳሙ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ አክብሮት የሚሰጠው ቅዱስ ስፍራ በመሆኑ በርካታ በሺዎች የሚቆጠሩ የሃይማኖቱ ተከታዮችና ጎብኚዎች በየዓመቱ ጥቅምትና መጋቢት 5 ቀን በስፍራው ይታደማሉ፡፡  ይህ ገዳም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምስራቅ ጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ በሰዋቲና ገዳም ቀበሌ ገ/ማህበር ልዩ ስሙ ምድረ ከብድ በተባለው ቦታ ይገኛል፡፡

ይህ ገዳም ከአዲስ አበባ በ122 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡ ይህም ማለት ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ የሚወስደው ዋናው መንገድ እስከ ቡኢ 104 ኪሎ ሜትር አስፋልት ሲሆን 18 ኪሎ ሜትር ግን ከዋናው መንገድ ወደ ግራ በመታጠፍ ፒስታ /ጥርጊያ/ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡

የአካባቢው አየር ጠባይ ወይን አደጋ ሲሆን ገዳሙ ረጅም ዕድሜ ማስቆጠሩ የተፈጥሮ ዛፎች ማለትም ዕድሜ ጠገብ የሆኑ በወይራ፣ በጽድና በዝግባ የተከበበ ስለሆነ ነፋሻማና ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ አለው፡፡

የምድረ-ከብድ ገዳም በ1014 ዓ.ም በአፄ እንድርያስ ዘመነ መንግስት በግብፃዊው አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ እንደተገደመ ይነገራል፡፡ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ከደቡብ ግብጽ ሜሳ ተብላ ከምትጠራው ቦታ ተወልደው የ3 ዓመት ልጅ እያሉ በአባ ዘመድ ብርሃን አስተዳደር ይመራ ወደነበረው ታላቅ ገዳም መግባታቸውን ገድላቸው ያስረዳል፡፡
በገዳሙ ውስጥ ይሰጥ የነበረውን ማዕረግ ቅስናን ከብፁ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብረሃም እንደ እንጦርስ ሥርዓት አስኬማንና ማዕረግ ቅስና የሚባሉ መንፈሳዊ ትምህርቶችን አጠናቀው በግብጽ ገዳማት ለ300 ዓመታት ተዘዋውረው ማስተማራቸውን ከገድላቸው ለመረዳት ችለናል፡፡
ከዚህ በኋላ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ በ60 አናብስትና በ60 አናብርት በተፈቀደላቸው የብርሃን ሰረገላ ታጅበው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ምድረ-ከብድ ገዳምን ባርከው መግባታቸውን ገድለ ገብረ-መንፈስ ቅዱስ ያስረዳል፡፡
የገዳሙ የምስረታ ጊዜን በተመለከተ የተለያዩ መረጃ ሰጪዎችና የጽሑፍ ድርሳናት በተለያየ ጊዜ ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም ግማሾቹ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተመሠረተ ሲሉ የተወሰኑት ደግሞ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚሉም አሉ፡፡
ምድረ-ከብድ የሚለው ስያሜ ምድረ-ከብድ ከሚል የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጓሜውም ጽኑ ፣ ታላቅ ፣ ልዩ፣ ከፍ ያለ ተራራማ ፣ የክብር፣ የከበደ ቦታ ማለት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ጥንታዊ ገዳም ውስጥ የመጀመሪያውን ቤተ-ክርስቲያን ያሠሩት ንጉስ እንድርያስ ሲሆኑ ለገዳሙ መተዳደሪያ ይሆን ዘንድ 280 ጋሻ መሬት መስጠታቸውም ይወሳል፡፡
የገዳሙ ሌላኛው ቤተ-ክርስቲያን በአፄ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት በፊት አውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ የተሠራ ሲሆን ቆርቆሮ የለበሰው ግን በ1920ዎቹ ዓ.ም በንግስት ዘውዲቱ አማካይነት እንደሆነ ይነገራል፡፡
አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ከምድረ-ከብድ ወደ ዝቋላ ይመላለሱበት እንደነበረ የሚነገርለት ዋሻ ከገዳሙ በስተ ምስራቅ በኩል ከቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ዋሻ የአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ሰረገላ ይባላል ብለው መረጃ ሰጪያችን ገልፀውልናል፡፡
አቡነ-ገ/መንፈስ ቅዱስ ለ562 ዓመታት ከቆዩ በኋላ መጋቢት 5ቀን ማረፋቸውና ቀብራቸውም እዛው ምድረ-ከብድ ገዳም ላይ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡
የምድረ-ከብድ ገዳም ብዙ ውጣ ውረድ ያጋጠመው ገዳም ነው፡፡ እነዚህም በአህመድ ግራኝና በጣሊያን ወረራ የደረሰበት ውድመት የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡
በግራኝ ወረራ ወቅት ብዙ ቤተ -ክርስቲያንና ነዋየ ቅድሳት የተቃጠሉበት ዘመን እንደሆነ በታሪክ የምናውቀው ሃቅ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ምድረ-ከብድ ገዳም ተመሣሣይ ጥፋት ደርሶበታል፡፡
ሌላኛው ደግሞ በጣሊያን ወረራ ወቅት ከ300 በላይ የገዳሙ ምዕመናን በውስጡ እንዳሉ በፋሺስቶች እንደታረዱ ይነገራል፡፡ የምድረ-ከብድ አቦ ገዳም ከ970 ዓመት ዕድሜ በላይ ያስቆጠረ ጥንታዊ ገዳም እንደሆነ ይነገራል፡፡

የምድረ-ከብድ አቦ ገዳም የውስጥ ይዘትን ሁኔታ በተመለከተ በጥቂቱ ስናስቃኛችሁ ገዳሙ በጠቅላላው በቁጥር 4 የሚሆኑ አነስተኛ ሊባሉ የማይችሉ ግቢዎች አሉት፡፡

እነዚህም ግቢዎች፡-

  1. የቤተ-ክርስቲያን ግቢ፡- ይህ ግቢ ዋና ግቢ ሲሆን ከሁሉም የበለጠ ሰፊ ግቢ ነው፡፡ እንዲሁም ጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን የሚገኝበት ነው፡፡
  2. የእንግዳ ማረፊያ /መቀበያ/ ግቢ ፡- ይህ ግቢ የታላላቅ አባቶችና ጳጳሳት መቀበያ /ማረፊያ /ግቢ ነው ፡- ይህ ግቢ አዲስ አበባ በሚኖሩ የአካባቢ ተወላጆች የተሠራ ግቢ ነው፡፡ በዚህ ግቢ ውስጥ 12 የመኝታ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የመታጠቢያ ክፍሎችና የምግብ መመገቢያ አዳራሽ እዚህ ጊቢ ውስጥ ይገኛል፡፡
  3. የመምህራን መቀመጫ ግቢ ፡- ይህ ግቢ የጎተራ እና ልዩ ልዩ ሥራዎች የሚከናወኑበት ግቢ ነው፡-
  4. የመናኒያን ግቢ ፡- ይህ ግቢ ብዙ ሥራ የሚከናወንበት ሲሆን የጠቅላላው የገዳሙ ማህበረሰብ ምግብ የሚዘጋጅበት ፣ ከብቶችና በጎች የሚረቡበትና እንዲሁም ደናግል መነኮሳት የሚኖሩበት ግቢ ነው፡፡
አቦ1